ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ''ጉዞ ወደ አገር ቤት'' የተሰኘ የክረምት ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ''ጉዞ ወደ አገር ቤት'' የተሰኘ የክረምት ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 29/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ''ጉዞ ወደ አገር ቤት'' የተሰኘ የክረምት ፌስቲቫል ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2016 ሊያካሂድ ነው።
የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወንድወሰን ግርማ በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በርካቶች በሦስት ምዕራፍ ወደአገራቸው ገብተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ሁለተኛው ትውልድ የሚሳተፉባቸው በርካታ ሁነቶች እየተካሄዱ መሆኑን ገልፀው፤ የሦስተኛው ምዕራፍ ጥሪ 'አሻራውን ያኑሩ የዕረፍት ጊዜዎች ያጣጥሙ' በሚል መሪ ኃሳብ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከጳጉሜን 3 ቀን ጀምሮ እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም በአድዋ ድል መታሰቢያ በሚካሄደው የክረምት ፌስቲቫልም የተለያዩ ትርኢቶችና ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚኖሩ ገልፀው በዚህም ሁለተኛ ትውልድ በስፋት እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
በሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ጥሪ አስካሁን ከ100 ሺህ በላይ ዳያስፖራዎች ወደአገር መግባታቸውን ገልፀው በአካባቢ ጥበቃ፣ በችግኝ ተከላ፣ በደም ልገሳና ሌሎች በጎ አድራጎት ሥራዎች ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
የዳያስፖራ ጥሪዎች አገር ከዳያስፖራው የምትፈልገውን ወረቶች ለማግኘት የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቅሰው እውቀት፣ ክህሎት፣ ቴክኖሎጂና ለንግድና ኢንቨስትመንት የሚያስፈልግ ካፒታል እንዲሁም ሬሚታንስ ለማግኘት ያስችላል ነው ያሉት።