በከተማው የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ  ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ለማስተካከል የሚስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተገለጸ

ጎንደር፤ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፦በጎንደር ከተማ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል በአዲሱ በጀት ዓመት በትኩረት እንደሚከናወን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ገለጹ። 

''ማገልገል ክብር ነው'' በሚል መሪ ሃሳብ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ላበረከቱ የመንግስት ሰራተኞች እውቅና ተሰጥቷል።

የከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ ሰራተኛው የአገልጋይነት መንፈስ በመላበስ ህዝብና መንግስት የጣለበትን ሃላፊነት በብቃትና ታማኝነት ሊወጣ ይገባል፡፡

በአዲሱ የበጀት ዓመት የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን ለመፍታት በላቀ ቁርጠኝነት እንደሚሰራና ሰራተኛውም በተመደበበት ዘርፍ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥብቅ የክትትል ስርዓት እንደሚተገበር  ገልጸዋል።

የመንግስት የስራ ሰዓትን መሸራረፍ፣ አገልግሎትን በገንዘብ መሸጥና ባለጉዳዮችን ማጉላላት የሚስተዋሉ የሰራተኛው የስነ ምግባር መጓደሎች በአዲሱ በጀት ዓመት ትኩረት ተሰጥቶ የማስተካከያ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ አስታውቀዋል።  

የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በከተማው የተጀመሩ ነባርና አዲስ የልማት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የሰራተኛው ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የመንግስት አገልግሎትን በፍትሃዊነት ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ የሲቪል ሰርቫንቱ ሚና የጎላ ነው  ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ፋሲል አብዩ ናቸው፡፡

በእውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት የዳበረ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት የመንግስትን የአገልግሎት አሰጣጥ ፈጣን ቀልጣፋና ፍትሃዊ ለማድረግ እንደሚያግዝም አስረድተዋል።

ለዚህም አዲሱን የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በተሟላ መንገድ ለመተግበር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

በአዲሱ የበጀት ዓመት ለሰራተኛው የማትጊያ ስርዓቶች እንደሚተገበሩ ጠቁመው፤ የስነ ምግባር ጉድለት በሚታይባቸው ሰራተኞች ላይ የህግ ተጠያቂነት አሰራሮች እንደሚኖሩ አመልክተዋል፡፡

የተሰጠው እውቅናም በሰራተኞች ዘንድ ተነሳሽነትን በመፍጠር ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።


 

የከተማው ገንዘብ መምሪያ ባልደረባ አቶ ፍሰሃ እሸቴ በሰጡት አስተያየት፤ የመንግስት ሰራተኞች የህዝብ አገልጋይ እንደመሆናችን አሰራርና ደንቦችን በማክበር ባለጉዳዮችን በአግባቡ የማስተናገድ ሃላፊነት አለብን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የመንግስት ሰራተኞች የስራ ሰዓትን በማክበር  ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል አለብን ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ የስራ ባልደረባ ሲስተር ዘነበወርቅ ንጋቱ ናቸው።

በመድረኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማትና ሰራተኞች እውቅና የተሰጠ ሲሆን ፤ በስነ-ስርዓቱ ላይ  በየደረጃው የሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላት ተገኝተዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም