በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ አለ- ዶ/ር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 29/2016 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ መኖሩን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በቻይና ቤጂንግ እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮ-ቻይና ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በኢትዮጵያ የፋርማስቲካል ዘርፍ ብቻ በዓመት ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገበያ መኖሩን አንስተው መንግስት በጤናው ዘርፍ ስድስት ዋና ዋና ዘርፎችን በመለየት አስፈላጊውን መሰረተ ልማት በማሟላት እየሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።



 

እነዚህም ሜድካል ቱሪዝምን ማዕከል ያደረገ የተሪሸሪ ጤና አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የድያግኖስትክ አገልግሎት፣ የህክምና ግብዓቶች ማምረቻ፣ የጤናው ዘርፍ የሰው ኃይል ልማት፣ የቅድመ ድንገተኛ ህክምና አገልግሎት፣ የጤና ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን መሆኑን አብራርተዋል።

በጤናው ዘርፍ በተለዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሳተፉ የመንግስት ማበረታቻዎችን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓትን በመዘርጋት አስተማማኝ የገበያ ሁኔታ እንዲመቻች እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም