ጉዞ ወደአገር ቤት የክረምት ፌስቲቫል ጳጉሜ 3 በአድዋ ሙዚየም ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
ጉዞ ወደአገር ቤት የክረምት ፌስቲቫል ጳጉሜ 3 በአድዋ ሙዚየም ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፦ጉዞ ወደአገር ቤት የክረምት ፌስቲቫል ከጳጉሜ 3 ቀን 2016 ጀምሮ በአድዋ ሙዚየም ይካሄዳል።
ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን የተዘጋጀ ''ጉዞ ወደአገር ቤት'' የተሰኘ የክረምት ፌስቲቫል ከጳጉሜ 3 እስከ 5 ቀን 2016 ድረስ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ዳያስፓራ አገልግሎት አስታውቋል።
ፌስቲቫሉን አስመልክቶ የአገልግሎቱ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወንድወሰን ግርማ በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በርካቶች በሶስት ምዕራፍ ወደ አገራቸው ገብተዋል።
ሶስተኛው ትውልድ የሚሳተፉባቸው በርካታ ሁነቶች መዘጋጀታቸውን ገልፀው፤ ከጳጉሜ 3 ቀን ጀምሮ የሚካሄደው ፌስቲቫል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
በፌስቲቫሉ የፋሽን ትርዒት፣ የስፖርት ውድድሮች፣ ኤክስፖና ሌሎች ተግባራት መካተታቸውንም ተናግረዋል።