ኮንትሮባንድና ንግድ ማጭበርበርን ትርጉም ባለው መልኩ የመቀነስ ስራ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል- አቶ ተስፋዬ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
ኮንትሮባንድና ንግድ ማጭበርበርን ትርጉም ባለው መልኩ የመቀነስ ስራ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል- አቶ ተስፋዬ ዳባ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፦ ኮንትሮባንድና የንግድ ማጭበርበር በሀገር ላይ እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ጫና ትርጉም ባለው መልኩ የመቀነስ ስራ ልዩ ትኩረት እንደሚያሻው የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ ገለጹ።
በሃዋሳ እየተካሄደ የሚገኘው የ2016 በጀት ዓመት የኮንትሮባንድ፣ የታክስና የንግድ ማጭበርበር መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
በውይይቱ ላይ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የፍትህ ሚኒስቴር አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ በመድረኩ ላይ የኮንትሮባንድ እንዲሁም የታክስና የንግድ ማጭበርበር ተግባራት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እያደረሱ ያለውን ጉዳት በውል መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
አመራሮች ሕገ ወጥ ተግባራቱን ለመከላከል ከፍተኛ ስራ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አሰራሮችን በቴክኖሎጂ የታገዙ ለማድረግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።
ኮንትሮባንድና ንግድ ማጭበርበር በሀገር ላይ እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ጫና ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ ቀጣዩ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን የሕግ ተገዢነት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አዝዘው ጫኔ ኮንትሮባንድ ዋንኛ የሰላማችንና ኢኮኖሚያችን ጠንቅ በመሆኑ ሕገ ወጥ ድርጊቱን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ወጥነት ባለው መልኩ መጠናከር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የኮንትሮባንድ፣የታክስና የንግድ ማጭበርበር መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች ላይ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ በትኩረት እንደሚሰራ መናገራቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።