የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በአዲስ አበባ መካሄዱ በዘርፉ ልምድ ለመለዋወጥና ትብብር ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበበ እየተካሄደ ያለው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በከተሞች ልማትና እድገት ልምድ ለመለዋወጥና ትብብር ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተመላከተ።

የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም "ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063" በሚል መሪ ኃሳብ በአዲስ አበባ በአድዋ ሙዚየም መካሄድ ጀምሯል።

ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚካሄደው ይህ አህጉራዊ ፎረም የኢትዮጵያ ከተሞች ተሞክሯቸውን በማጋራት ከአቻ የአፍሪካ ከተሞች ጋር የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ነው።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ ዲን ደጉ በቀለ (ዶ/ር) ፎረሙ የከተሞችን እድገት፣ ዘመናዊነት፣ ከተሜነትን በጋራ ማረጋገጥ ዋነኛ ዓላማው ነው ብለዋል።


 

ፎረሙ ከተሜነትን በማረጋገጥ ውስጥ የሚገኙ መልካም እድሎች ለመጠቀምና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የጋራ መፍትሄ ማፈላለግ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአፍሪካ አገራት ተቀራራቢ የሆነ የከተማ እድገትና የከተሜነት ሂደት እንዳላቸው አንስተው ፎረሙ በዘርፉ ልምድ ለመለዋወጥና ለመቀመር ትልቅ እድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ትኩረት ከተሰጣቸው አጀንዳዎች መካከል ዘመናዊ ከተማን መገንባትና ከተሜነትን ማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ወደ ትላልቅ ከተሞች የሚደረግ ፍልሰትን በመግታት ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ከተሜነትን ለማስፋት ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ጉዳይ ላይ ለመምከርና ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ፎረሙ ሁነኛ መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በተጓዳኝም፤ መሆኑም የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በኢትዮጵያ መካሄዱ የአገሪቱን የቱሪዝም ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ነው ያሉት።

በተለይም ጎን ለጎን የሚካሄዱ ሁነቶች ለቱሪዝም ዲፕሎማሲ መጎልበት ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

አዲስ አበባ የመጀመሪያውን አህጉራዊ ፎረም ማዘጋጀቷ ተመራጭነቷን ከማጉላት በዘለለ በከተማዋ በራስ አቅም የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ለማሳየት ምቹ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

በተጨማሪም አቻ ከተሞች ከአዲስ አበባ የተግባር ልምድ ለመቅሰምና የጋራ ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ለማጎልበት ጥሩ ማሳያ ይሆናልም ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም