በክልሉ የኢንቨስትመንት ማሽነሪዎችን በራስ አቅም ወደ ክልሉ ላስገቡ 189 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት መሬት ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የኢንቨስትመንት ማሽነሪዎችን በራስ አቅም ወደ ክልሉ ላስገቡ 189 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት መሬት ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል
መቀሌ፤ ነሀሴ 29/2016 (ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል የኢንቨስትመንት ማሽነሪዎችን በራስ አቅም ወደ ክልሉ ላስገቡ 189 ባለሃብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያስችል የኢንቨስትመንት መሬት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ባለሃብቶች በበኩላቸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ የኢንቨስትመንት መሬት ማሻሻያ ማድረጉ በቀጣይ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ስራዎችን ለማስፋፋት ለያዙት ዕቅድ መሳካት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል መኮንን እንደገለፁት፤ በክልሉ ልማት ለመሳተፍ 189 ባለሃብቶች ከ77 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያደርግ መሬት ተዘጋጅቷል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሃብቶችን ወደ ክልሉ ለመሳብና ዘርፉን ለማበረታታት የመሬት አሰጣጥ መመሪያ እንዲሻሻል ማድረጉን አስታውሰዋል።
ከተደረጉት ማሻሻያዎች መካከል ለኢንቨስትመንት የሚሆኑ ማሽነሪዎችን በራሳቸው ገንዘብ ለሚያስገቡ ባለሃብቶች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የኢንቨስትመንት መሬት በሊዝ መነሻ ዋጋና ያለ ጨረታ እንዲሰጥ የሚደነግግ ህግ ማውጣቱን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
እንዲሁም ማሻሻያው ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ይዘው በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የካፒታሉን ገንዘብ 10 በመቶ በዝግ ሂሳብ ካስቀመጡ የመስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው የሚያደርግ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
ኮሚሽኑ ከ91 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሃብቶች በጥር ወር 2016 ዓ.ም ጥሪ ማቅረቡንም አስረድተው በጥሪው መሰረትም የመሬት አቅርቦት ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል።
በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ 189 ለሚሆኑ ባለሃብቶች በቅርቡ መሬት መስጠት እንደሚጀምርም ኮሚሽነሩ አክለው ገልፀዋል።
ለኢንቨስትመንት የሚሆን መሬት በወቅቱ ባለማግኘታቸው ማሽነሪዎችን አስገብተው በኪራይ መጋዘን በመስራት ላይ ካሉትና በሁለት ባለሃብቶች ሽርክና የተመሰረተው ፍቅረ እና ሃይለ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች አንዱ ነው።
የኩባንያው ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቅረ ሃይለ እንደገለፁት፤ እስካሁን ለስራው የሚሆን መሬት ባለማግኘታቸው በየወሩ ለመጋዘን ኪራይ 30 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ ለመስራት መገደዳቸውን ያስረዳሉ።
መንግስት ችግራቸውን ተገንዝቦ የመስሪያ ቦታ የሚያገኙበትን ሁኔታ እያመቻቸ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ፍቅረ፣ በቀጣይ ዕድሉን ካገኙ ስራውን የማስፋፋት ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከሶስት ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን እስከ አንድ ቢሊዮን ብር በሚደርስ ወጪ የብረታ ብረት ፋብሪካ ለመገንባት የመሬት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ የሚገኙት አቶ ሳምሶም ገብረእግዚአብሄር በ250 ሚሊዮን ብር ወጪ ማሽነሪዎች ማስገባታቸውን ይናገራሉ።
ከውጭ የሚገቡ የብረታ ብረት ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችሉ ምርቶችን የሚያመርትና እስከ 150 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር አቅደው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው፤ በየወሩ እስከ 70 ሺህ ብር ለኪራይ ወጪ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመሬት አቅርቦት ላይ በቅርቡ ባሻሻለው የመሬት አሰጣጥ መመሪያ መሰረት ኩባንያቸው የዕድሉ ቅድሚያ ተጠቃሚ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ መሬት ለማግኘት ተስፋ ማድረጋቸው አመልክተዋል።