ቀጥታ፡

የቻይናው ቶዮ ሶላር ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፦መቀመጫውን ቬተናም ያደረገው ቶዮ ሶላር የተባለ የቻይና ኩባንያ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስር በሚገኙ የኢንቨስትመንት ማዕከላት ገብቶ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) የቶዮ ሶላር ዋና ስራ አስኪያጅ ሊ ሁያንግን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ውስጥ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ፤መሰረተ ልማቶችን ፤ የተለያዩ የኢንቨስመንት ማበረታቻዎችን እንዲሁም በመንግስት በኩል የተደረጉ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሞች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል ።

በቀጣይም ኩባንያው የቅድመ ኢንቨስትመንት ምልከታውን አጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡

የቶዮ ሶላር ዋና ስራ አስኪያጅ ሊ ሁያንግ በበኩላቸው ኩባንያቸው ስለ ኢንቨስትመንት እቅዱ እንዲሁም ኩባንያው ያለበትን ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴና በመጀመሪያ ምዕራፍ ሊያከናውናቸው ባቀዷቸው ስራዎች ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል።

ኩባንያው ወደ ስራ ሲገባም በመጀመሪያው ምዕራፍ 5 ሄክታር የለማ መሬት ተረክቦ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርግ የተገለፀ ሲሆን ከ400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም በቋሚነት የስራ እድልን የሚፈጥር ይሆናል ተብሏል።

መካከለኛው ምስራቅ ፤ ህንድና አሜሪካ የምርቶቹ መዳረሻ ገበያዎች እንደሚሆኑ መለየታቸውም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኩባንያው አመራሮች በቦሌ ለሚ ፤በሐዋሳና የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና የኢንቨስትመንት ማዕከላት ዉስጥ የቅድመ ኢንቨስትመንት ምልከታ እንደሚያደርጉም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም