የጳጉሜን ቀናት በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የጳጉሜን ቀናት በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፦የ2016 ዓ.ም አዲስ ዓመት ዋዜማ አምስቱ የጳጉሜን ቀናት በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በተለያየ ዝግጅትና ስያሜ በድምቀት ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ አስታወቁ።
ሚኒስትር ዴኤታው የ2017 ዓ.ም የአዲስ ዓመት ዋዜማ አምስቱ የጳጉሜን ወር ቀናት አከባበር ዝግጅትና ስያሜን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥተዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በሰጡት መግለጫ፥ ኢትዮጵያዊያን ለ2017 ዓ.ም የአዲስ ዓመት ዋዜማ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጳጉሜን ወር ቀናት ኢትዮጵያዊያን አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ የሚቀበሉበት የመሸጋገሪያ ድልድይ ናቸው ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የጳጉሜን ወር ቀናት የዜጎችን አንድነትና አብሮነት በሚያጎላ መልኩ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት መከበራቸውን አስታውሰዋል።
በዘንድሮው የ2017 ዓ.ም አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ አምስት የጳጉሜን ቀናትም በተለያዩ ደማቅ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
በዚህም "ጳጉሜን-1 የመሻገር፣ ጳጉሜን-2 የሪፎርም፣ ጳጉሜን-3 የሉዓላዊነት፣ ጳጉሜን-4 የሕብር እና ጳጉሜ-5 የነገ ቀን" በሚሉት አምስት ስያሜዎች በድምቀት እንደሚከበሩ ገልጸዋል።
ቀናቱም በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ በመላ ዓለማት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ኮሚኒቲ አባላት በድምቀት የሚከበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አምስቱ የጳጉሜን ቀናት ክብረ በዓልም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቋቋም በለውጡ መንግስት የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል ዓላማ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።