ኢትዮጵያ በዓለም ከ20 ዓመት በታች ያስመዘገበችው ውጤት በአትሌቲክሱ ዘርፍ ታዳጊዎች ያላቸውን እምቅ አቅም ያመላከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም ከ20 ዓመት በታች ያስመዘገበችው ውጤት በአትሌቲክሱ ዘርፍ ታዳጊዎች ያላቸውን እምቅ አቅም ያመላከተ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፦በዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ውጤት ታዳጊዎች ላይ ያለውን እምቅ አቅም ያመላከተና የስፖርት ዲፕሎማሲን ያነቃቃ ነው ሲሉ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገለፁ።
በዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን የዕውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቡት ውጤት ታዳጊዎች ያላቸውን እምቅ አቅም ያመላከተ ነው ብለዋል።
የስፖርቱ ማህበረሰብ ይህንን ከግምት ያስገባ ተግባር በስፋት መከናወን እንዳለበት በአንክሮ ሊገነዘቡት ይገባል ብለዋል።
የታዳጊዎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የአሸናፊነት ምክንያት ኢትዮጵያውያን በየሄዱበት ማሸነፍ ይችላሉ፤ የሚል ስሜት ዳግም በዓለም ኀብረተሰብ ዘንድ የፈጠረ ነው ሲሉም አክለዋል።
ድሉ ለስፖርት ዲፕሎማሲው ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ሲሉ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ በዓለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የተመዘገበው ውጤት በእ.አ.አ በ2025 ቶኪዮ ላይ ለሚደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሞራል የሚሆን ነው ብላለች።
በቀጣይም ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ያላትን ስም ለመመለስ በትኩረት ይሰራል ስትልም ተናግራለች።
በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ከዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዞ ላጠናቀቀው ልዑክ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ሽልማት ተበርክቶለታል።
ወርቅ ላመጡ አትሌቶችና አሰልጣኞች 40 ሺህ ብር፣ ብር ላመጡ አትሌቶችና አሰልጣኞች 25 ሺህ ብር፣ ነሐስ ላመጡ አትሌቶችና አሰልጣኞች 15 ሺህ ብር፣ ዲፕሎማ ላመጡ አትሌቶችና አሰልጣኞችየ10 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ውድድሩ ላይ ለተሳተፉ አትሌቶች የ5ሺህ ብር ሽልማት ሲበረከት፣ ለቡድኑ የቴክኒክ ቡድን መሪ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱና ለቡድን መሪዋ አትሌት መሰለች መልካሙ ለእያንዳንዳቸው የ35 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ከነሐሴ 21 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በፔሩ ሊማ በተደረገው ሻምፒዮናን ኢትዮጵያ 6 የወርቅ፣ 2 የብርና 2 የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎች በማግኘት አሜሪካን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በሁለቱም ፆታዎች 19 አትሌቶች ያሳተፈች ሲሆን በሻምፒዮናው በ8 መቶ ፣ 1 ሺህ 500፣ 3 ሺህና በ5 ሺህ ሜትር በሁለቱም ጾታዎች፣ እንዲሁም በ10 ሺህ ሜትር እርምጃ እና በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል በሴቶች ውድድር አካሂደዋል።
በፔሩ ሊማ በተካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ሲገባም አቀባበል እንደተደረገለት የሚታወስ ነው ።