ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል በትምህርት ሽፋን የታየውን ለውጥ በጥራትም ለመድገም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል 

ጋምቤላ ፤ ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል በትምህርት ሽፋን የታየውን ለውጥ በጥራትም ለመድገም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  ዓለሚቱ ኡሞድ አስገነዘቡ።

‘‘በተደራጀ የህዝብ ተሳትፎ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ’’ በሚል መሪ ሃሳብ 13ኛው ትምህርት ጉባኤ በክልሉ ደረጃ  ዛሬ በጋምቤላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳድሯ የትምህርት ጉባዔውን ሲከፍቱ እንደገለጹት የአንድ ሀገር እድገትና ብልጽግና ሊረጋገጥ የሚችለው ዘመኑ በሚጠይቀው ዕውቀትና ክህሎት የተገነባ ዜጋ ማፍራት ሲቻል ነው።

ባለፉት ዓመታት በጋምቤላ ክልልም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ሽፋንን  በማረጋገጥ ረገድ የተሻለ ለውጥ መመዝገቡን አስታውሰዋል።

ይሁንና በትምህርት ቤቶች የመሰረተ ልማትና ሌሎች የግብዓት ችግሮች እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በትምህርት ጥራት በኩል በርካታ ስብራቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለትምህርት ጥራት ተግዳሮት የሆኑ የመሰረተ ልማትና የግብዓት ችግሮችን በመፍታት የታለመውን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥና ብቃት ያለው ዜጋ ለመገንባት ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በዕለቱ የተጀመረው 13ኛ የትህምርት ጉባዔ ለቀጣይ 2017 የትምህርት ዘመን ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች የሚነሱበት መድረክ በመሆኑ ታዳሚዎች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸውም ርዕሰ መስተዳድሯ አሳስበዋል።


 

በጉባዔው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አበበ እንዳሉት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ትብብር የሚጠይቅ ቢሆንም  ከዘርፉ አመራርና ሙያተኞች የላቀ ቁርጠኝነትን ይፈለጋል።

ስለሆነም እንደ ሀገር ለታለመው የትምህርት ጥራት መረጋገጥ የትምህርት አመራር አካላት፣ መምህራንና ሌሎች አጋር አካላት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

  የክልሉ መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለጀመረው ዘርፈ ብዙ ስራዎች መቀናት ማህበራቸው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም አቶ ሽመልስ አስታወቀዋል።


 

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ላክደር ላክባክ በበኩላቸው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ተግባር ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ለትምህርት ጥራቱ ስብራት መንስዔ ሆነው ከተለዩት ምክንያቶች መካከል የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማቶችና የግብዓት እጥረት ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በመሆኑም የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታትና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሁሉም ተባበሪ አካላት ድጋፍና ትብብር እንዲታከልበት አቶ ላክደር ጠይቀዋል።

በትምህርት ጉባዔው ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የትምህርት የአመራር አካላት፣ ባለሙያዎች፣ የወላጅ ተማሪ መምህር ህብረትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም