ሀገራዊ ምክክሩ የሚስተዋሉ የሃሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ያመጣል -የሀገር ሽማግሌዎች

አርባ ምንጭ ነሐሴ 29/2016 (ኢዜአ):-  ሀገራዊ ምክክሩ የሀሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚያስችል ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎፋና ጋሞ ዞኖች የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

የጎፋ ዞን ሀገር ሽማግሌ አቶ ጊያ ግዛው ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ ቁርሾዎችና አለመግባባቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ዕድገትን ለማረጋገጥ ምቹ መደላድልን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ምክክሩ በተለይ ዘመናትን የተሻገሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን በዘላቂነት በመፍታት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እጅግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የለውጡ መንግስት በኢትዮጵያ ታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየትና በመመካከር ለመፍታት ያሳየው ቁርጠኝነት የሚያስመሰግነው ተምሳሌት ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክሩግጭቶችን በዘላቂነት በመፍታት ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል ትልቅ መሣሪያ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የጎፋ ዞን የሀገር ሽማግሌ አቶ ሀብታሙ ገብረጻድቅ ናቸው።


 

ሁሉንም ማህበረሰብ ባሳተፈ መልኩ በየደረጃው የሚካሄደው ምክክር ሰላምን ለማጽናትና የኢትዮጵያን ዕድገት ለማረጋገጥ ይረዳል ብለዋል።

በጠረጴዛ ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ ወደ መመካከር መገባቱ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄን የሚያስገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የጋሞ ዞን የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ተፈራ ኦይቻ በበኩላቸው ሀገራዊ የምክክር ሂደት በዘመናት ሂደት ያለመግባባት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣትና በመመካከር ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል።


 

ምክክሩ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ጠንካራ አንድነትን ለመፍጠር መሰረት መሆኑን ጠቅሰው የአካባቢያችንን የውይይት ዕሴቶች በመጠቀም የምክክር ኮሚሽን ተግባራትን ማገዝ እንንደሚገባ ገልጸዋል።

ሌላኛው የጋሞ የሀገር ሽማግሌ አመለ አልቶ ምክክርና ውይይት ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የጋሞ ማህበረሰብ በተቃርኖ ያሉ ወገኖችን ወደ ውይይት በማምጣት ችግርን የመፍታት የዳበረ ልምድ አለው ብለዋል።

የሀገር ሽማግሌዎቹ ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም