በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የቀበሌና የወረዳ አስተዳደር አደረጃጀት ህዝቡ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኝ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የቀበሌና የወረዳ አስተዳደር አደረጃጀት ህዝቡ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኝ ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የቀበሌና የወረዳ አስተዳደር አደረጃጀት ህዝቡ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በኦሮሚያ ክልል አዲስ የቀበሌና የወረዳ አስተዳደር አደረጃጀት ስራ ላይ በመዋል ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።
ይህን በማስመልከት በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሃላፊው በመግለጫቸው አዲሱ አደረጃጀት የአገልግሎት አሰጣጥን የማሻሻል፣ ሰላምን የማስፈን እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቅርበት የመፍታት ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በክልሉ አዲስ የተዋቀረው የቀበሌ መዋቅር በ1967 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ከተደራጀ ወዲህ መንግስትና ህዝብን የሚያቀራርብ ትልቅ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት እና ፓርቲው በክልሉ አዲስ የወረዳና የቀበሌ መዋቅር በመከለስ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ ምቹና ተደራሽ እንዲሆን በመስራት ላይ እንደሚገኙም አረጋግጠዋል፡፡
በአደረጃጀቱ ቀልጣፋና ምቹ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር ብሎም የህዝቡ ችግር በጥናት እና በእውቀት መፍትሔ እንዲያገኝ የሚያስችል ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
ህዝቡ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆንና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ህዝቡን ባሳተፈ ውይይት ምላሽ እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያም አደረጃጀቱ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
የአደረጃጀቱ ተግባራዊ መደረግ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣም ትልቅ ዕድል ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ የህዝቡን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመስራት ላይ የሚገኝ ፓርቲ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱም እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡