ኢትዮጵያ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ምሳሌ የሚሆን ሥራ እየሰራች ነው - ጫልቱ ሳኒ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ምሳሌ የሚሆን ሥራ እየሰራች ነው - ጫልቱ ሳኒ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ምሳሌ የሚሆን ሥራ እየሰራች ነው ሲሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ገለፁ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቲ ሳኒ በመድረኩ፤ ኢትዮጵያ ፎረሙን እንድታዘጋጅ ከተመረጠች ጀምሮ አስፈላጊውን ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል።
ፎረሙ በአፍሪካ በከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በትብብርና በቅንጅት ለመፍታት የድርሻችንን የምንወጣበት ነው ብለዋል።
ለአፍሪካ 2063 አጀንዳ እውን መሆን የከተሞችን ዘላቂ ልማት ማረጋገጥና የክትመት ምጣኔውን ማጣጣም ይገባል፤ ለዚህም መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
በአፍሪካ እየጨመረ ላለው የሕዝብ ቁጥርና የአየር ንብረት ተጽዕኖ ምላሽ መስጠት የሚችል የከተሞች ዘላቂ ልማት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ከተሞች ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ምሳሌ የሚሆኑ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።