በአለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፈው ልዑካን ቡድን የገንዘብና የእውቅና ሽልማት ተበረከተለት - ኢዜአ አማርኛ
በአለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፈው ልዑካን ቡድን የገንዘብና የእውቅና ሽልማት ተበረከተለት
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፦ በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዞ ላጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን የእውቅናና የገንዘብ ሽልማት ተበረከተለት።
በፔሩ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ላጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን የዕውቅና መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የዕውቅና መርሐግብሩ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉና የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ልዑካን ቡድኑ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ሽልማት እንደተበረከተለትም ተገልጿል።
በዚህም ወርቅ ላመጡ አትሌቶችና አሰልጣኞች 40 ሺህ ብር፣ ብር ላመጡ አትሌቶችና አሰልጣኞች 25 ሺህ ብር፣ ነሐስ ላመጡ አትሌቶችና አሰልጣኞች 15 ሺህ ብር፣ ዲፕሎማ ላመጡ አትሌቶችና አሰልጣኞችየ10 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ውድድሩ ላይ ለተሳተፉ አትሌቶች የ5ሺህ ብር ሽልማት ሲበረከት፣ ለቡድኑ የቴክኒክ ቡድን መሪ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱና ለቡድን መሪዋ አትሌት መሰለች መልካሙ ለእያንዳንዳቸው የ35 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ከነሐሴ 21 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በፔሩ ሊማ በተደረገው ሻምፒዮናን ኢትዮጵያ 6 የወርቅ፣ 2 የብርና 2 የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎች በማግኘት አሜሪካን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በሁለቱም ፆታዎች 19 አትሌቶች ያሳተፈች ሲሆን በሻምፒዮናው በ8 መቶ ፣ 1 ሺህ 500፣ 3 ሺህና በ5 ሺህ ሜትር በሁለቱም ጾታዎች፣ እንዲሁም በ10 ሺህ ሜትር እርምጃ እና በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል በሴቶች ውድድር አካሂደዋል።
በፔሩ ሊማ በተካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ሲገባም አቀባበል እንደተደረገለት የሚታወስ ነው ።