ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ከታንዛንያ ጋር ታደርጋለች

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 29/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከታንዛንያ አቻው ጋር ያካሄዳል።

የሁለቱ አገራት ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰዓት 60 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ይከናወናል።

በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ 48 አገራት በ12 ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ በማጣሪያው በምድብ 8 ከጊኒ፣ታንዛንያና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር መደልደሏ ይታወቃል።

ዋልያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከታንዛንያ ጋር ያደርጋሉ።

የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በመጀመሪያ ዙር ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ ካደረጉ በኋላ ቡድኑ የአገር ቤት ልምምዱን በአዳማና አዲስ አበባ አከናውኗል።

ብሔራዊ ቡድኑ በታንዛንያ ለሚያደርጋቸው ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን ይዞ ከትናንት በስቲያ ታንዛንያ መግባቱ ይታወቃል።

ተጫዋቾቹ ላለፉት ሁለት ቀናት በታንዛንያ ልምምዳቸውን አድርገዋል። ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ጨዋታው በሚደረግበት የታንዛንያ ብሔራዊ ስታዲየም ትናንት አከናውኗል።

በ54 ዓመቱ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሄሜድ ሱሌይማን የሚመራው የታንዛንያ ብሔራዊ ቡድን ላለፈው አንድ ሳምንት ገደማ ዝግጅቱን በዳሬ ሰላም ሲያደርግ ቆይቷል።

ኢትዮጵያና ታንዛንያ ከዚህ ቀደም የውድድርና ወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ 23 ጊዜ ተገናኝተዋል።

ኢትዮጵያ 10 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን የያዘች ሲሆን ታንዛንያ 6 ጊዜ አሸንፋለች። 7 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

በፊፋ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ 143ኛ እንዲሁም ታንዛንያ 113ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የ40 ዓመቱ ሴኔጋላዊ ኢሳ ሲይ የሁለቱን አገራት ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛና የሜዳ ጨዋታውን ጳጉሜ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ዳሬ ሰላም በሚገኘው ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም (የታንዛንያ ብሔራዊ ስታዲየም) ያከናውናል።

ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ 8 የሚገኙት ጊኒና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አርብ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም ኪንሻሳ ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 24 አገራት ተሳታፊ መሆናቸውን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም