ስራ ፈጣሪ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያግዝ ስልጠና እየወሰድን ነው - የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት አሰልጣኞች ስልጠና ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ስራ ፈጣሪ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያግዝ ስልጠና እየወሰድን ነው - የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት አሰልጣኞች ስልጠና ተሳታፊዎች
አሶሳ፤ ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ):- ስራ ፈጠሪ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያግዝ ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውን ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት አሰልጣኞች ስልጠና ተሳታፊዎች ተናገሩ፡፡
"ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት" በሚል መሪ ሐሳብ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሀገሪቷ ባሉ 17 ዩኒቨርሲቲዎች ለአሰልጣኝ መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።
ስልጠናው በቴክኒክና ሙያ፣ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ በተዘጋጁ ፖሊሲዎችና አዳዲስ እሳቤዎች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ባለው ስልጠና እየተሳተፉ የሚገኙ ሰልጣኞች ለኢዜአ እንደገለጹት ስልጠናው አዳዲስ እሳቤዎችንና ፖሊሲዎችን ከማስገንዘቡም በላይ ተመልሰው በሚያካሄዱት የዘርፉ ስልጠና ሥራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችላቸው ነው።
ከሰልጣኝ አመራሮች መካከል በአሶሳ ግብርና ኮሌጅ የዕፅዋት ሳይንስ ትምህርት ክፍል አሰልጣኝ ሀብታሙ ካሳ እንዳሉት ስልጠናው ስራ ፈጣሪ እና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የሚያግዝ ነው፡፡
በስልጠናው የተግባቦት ክህሎታቸውን ተጠቅመው በቀሰሙት እውቀት አምራች እና ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት እንዲችሉም ከሙያ በተጨማሪ የኮሙኒኬሽን ክህሎታቸውን ለማጎልበት የሚያስችል ግንዛቤ ማግኘታቸውን አቶ ሀብታሙ ጠቁመዋል፡፡
በካማሽ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ የኮንስትራክሽን አሰልጣኝ ዘገዬ ምህረት በበኩላቸው ስልጠናው በክህሎት እና ዕውቀት የታነፁ ሰልጣኞችን ከማፍራት በተጨማሪ ኮሌጆች በራሳቸው አምራች እንዲሆኑም ጭምር ትልቅ ትምህርት ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው ከሌሎች ሰልጣኞች ተሞክሮ የወሰዱበት እንዲሁም በቡድን ውይይት የተለያዩ ሃሳቦችን ያዳበሩበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች እስከ አሁን የነበሩበትን ደካማ የስልጠና አሰጣጥ ያሳየ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ ተሳታፊ የፓዌ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ድንቅነሽ በየነ ናቸው፡፡
ወደ ተቋማቸው ሲመለሱም የነበረውን የትምህርት እና ስልጠና አሰጣጥ ለማስተካከል እንደሚሰሩ ተናግረው፤ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት የሚፈጥር ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ የክህሎት እና ተቋማት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ዩሱፍ ያሲን እንዳብራሩት እየተሰጠ ያለው ሀገር አቀፍ ስልጠና በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በሁሉም ቦታ ተወዳዳሪ እና አምራች ኃይል ለማፍራት ይጠቅማቸዋል፡፡
በፌደራል የቴክኒክ እና ሙያ ኢንስቲትዩት የአመራር እና አስተዳደር ፋኩሊቲ ዲን እና የአሶሳ ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ በክረፅዮን ኃይለስላሴ (ዶ/ር) የስልጠናው ዓላማ ኮሌጆች በየዘርፉ ስራ ፈጣሪ የሰው ኃይል በማፍራት ኢትዮጵያ ለያዘቸው የስራ አጥ ቁጥር ቅነሳ ትልቁን ድርሻ እንዲወጡ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ ከስድስት የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት የተውጣጡ 344 የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች የአመራር አካላት እና አሰልጣኞች ስልጠናውን እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡