ኢትዮጵያ የቻይናን ያልተቋረጠ ዘርፈ-ብዙ ድጋፍ በእጅጉ ታደንቃለች- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የቻይናን ያልተቋረጠ ዘርፈ-ብዙ ድጋፍ በእጅጉ ታደንቃለች- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የቻይናን ያልተቋረጠ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ በእጅጉ ታደንቃለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ላደረጉልን ደማቅ አቀባበል እና ላካሄድነው ጠቃሚ ውይይት አመሰግናለሁ ሲሉ አስፍረዋል።
ኢትዮጵያ የቻይናን ያልተቋረጠ ዘርፈ-ብዙ ድጋፍ በእጅጉ እንደምታደንቅ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንደ ሀገር የተለያዩ ተግዳሮቶችን ብናስተናግድም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በቴሌኮሙኒኬሽንና ሌሎች ዘርፎች ትርጉም ያላቸው የለውጥ እርምጃዎች ተራምደናል ብለዋል።
በዚህ የእድገት ጎዳና የቻይና ኢንቨስትመንቶች ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል ሲሉም ገልጸዋል።
በቱሪዝም ብሎም በወረቀት እና እንደ ፐልፕ ያሉ ተያያዥ ግብዓቶች ኢንዱስትሪንም ለማሳደግ እምቅ አቅም አለ ብለዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር በጽናት እንሰራለን ሲሉም ገልጸዋል።