ቀጥታ፡

በክልሉ በንብ ማነብ ሥራ ላይ ለሚሰማሩ 433 አርሶ አደሮች የንብ መንጋና ዘመናዊ ቀፎ ድጋፍ ተደረገ

መቀሌ ፤ ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል ለተለያዩ ወረዳዎች በንብ ማነብ ሥራ ለሚሰማሩ 433 አባዎራና እማዎራ አርሶ አደሮች የንብ መንጋና ዘመናዊ ቀፎ ድጋፍ ማድረጉን በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን የትግራይ ቅርንጫፍ አስታወቀ።

አርሶ አደሮቹም በተደረገላቸው ድጋፍ ምርታማነትን በማሳደግ የተሻለ ህይወት ለመምራት እንደሚጥሩም ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የትግራይ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ዶክተር አብረሃ ኪዳነማርያም ለኢዜአ እንደገለፁት፤  ለአርሶ አደሮቹ በነፍስ ወከፍ ሶስት የንብ መንጋና ሶስት የዘመናዊ ቆፎዎች እንዲያገኙ ተደርጓል። 

በተጨማሪም የንብ ማነብ ሥራውን የሚያቀላጥፉ የተለያዩ ዘመናዊ መሳርያዎችንም ለአርሶ አደሩ መታደሉን ተናግረዋል።

 ለአርሶ አደሮች በድጋፍ መልክ የተሰጡ የንብ መንጋዎችና የዘመናዊ ቀፎዎች በጥቅሉ ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ እንደወጠባቸው ገልፀዋል። 


 

በጊዜያዊ አስተዳደሩ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የንብ፣ የሓር ትልና የዓሳ እርባታ ቡድን መሪ አቶ ጎሹ ወልደአብዝጊ በበኩላቸው፣ የተደረገው ድጋፍ አርሶ አደሮቹ ጠንክረው ሰርተው ህይወታቸውን በዘላቂነት ለመለወጥ መስፈንጠሪያ እንደሚሆን ተናግረዋል። 

በክልሉ ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ ንብ አናቢዎች እንዳሉ የገለፁት አቶ ጎሹ፣ "ጥራትና ብዛት ያለው ማር እያመረቱ ለገበያ በማቅረብ ራሳቸውንና ሀገራቸውን እየጠቀሙ ነው" ብለዋል። 

የንብ መንጋ እና ዘመናዊ ቀፎ ከተሰጣቸው አርሶ አደሮች መካከል በትግራይ ደቡባዊ ዞን በእምባ አለጀ ወረደ ዓይባ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አቶ አባዲ ሀዱሽ፣ መንጋ ንቦቹን በተሰጡኝ ዘመናዊ ቀፎዎች ተንከባክቤ በዓመት ሶስት ጊዜ ማር በማምረት ህይወቴን  ለመቀየር ዝግጁ ነኝ ብለዋል። 

"ድጋፉ ሴቶችን ግምት ውስጥ አስገብቶ በመተግበሩ ደስታ ተሰምቶናል" ያሉት ደግሞ በደቡባዊ ዞን እንዳመሆኒ ወረዳ መሀን ገጠር ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ንግስቲ ህሉፍ ናቸው።

"በተደረገልን ድጋፍ በመነሳሳት ሰርተን ውጤታማነታችንን ለማሳየት እንጥራለን" ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም