በዓለም ሻምፒዮናው የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከፍ በማድረግ ሀገርን አኩርታችኋል - ሸዊት ሻንካ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2016(ኢዜአ):- አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮናው የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከፍ በማድረግ ሀገርን አኩርታችኋል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።

በፔሩ ሊማ በተካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል።


 

ልዑካን ቡድኑ ማምሻውን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ አቀባበል ተደርጎለታል።

በዚሁ ወቅት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ አትሌቶች በፔሩ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባስመዘገባችሁት ድል የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ ሀገርን አኩርታችኋል ሲሉ ተናግረዋል።


 

ሚኒስትሯ አትሌቶች እንደ ሁልጊዜው በሻምፒዮናው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ በማድረግና ስሟ ደምቆ እንዲጠራ በማድረግ አኩሪ ድል ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በፔሩ የተገኘውን ድል በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች መድገም እንደሚገባም አመልክተዋል።

መንግስት ለአትሌቲክሱ ውጤታማነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ሁሌም ከስፖርቱ ጎን እንደሚቆም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ አትሌቶቹን ባስመዘገባችሁት አመርቂ ድል ኮርተንባችኋል፣ እንኳን ደስ አላችሁ ብላለች።


 

በሻምፒዮናው በ1500 ሜትር የወርቅና በ5000 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያገኘው አትሌት አብዲሳ ፈይሳ በውድድሩ ወቅት የነበረው ነፋሻማ አየር ፈታኝ ቢሆንም ያንን ተቋቁሞ ውጤት ማምጣት መቻሉን ገልጿል።

በ5000 ሜትር የነበሩብኝን ክፍተቶች በማረም በ1500 ሜትር ውድድር አሸናፊ መሆን ችያለሁ ሲል ተናግሯል።

በቀጣይ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን የማስጠራት ሕልም እንዳለው ጠቅሷል።

በ3000 ሜትር መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘው አትሌት ኃይሉ አያሌው በመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ተሳትፎው ባስመዘገበው መልካም ውጤት ደስተኛ መሆኑን ገልጾ ውድድሩ ጥሩ ልምድ የቀሰምኩበት ነው ብሏል።

በቀጣይ ያሉብኝን ክፍተቶች በመሙላት በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያን ስም ለማስጠራትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት አደርጋለሁ ሲል ገልጿል።

ለአትሌቲክስ ልዑካን ቡድኑ ዛሬ የእውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር እንደሚካሄድ ኢዜአ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ በፔሩ ሊማ በተካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት ሻምፒዮና በ 6 ወርቅ፣ 2 የብርና 2 የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አሜሪካን ተከትላ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የተሳትፎ ታሪኳ ከፍተኛውን ደረጃ ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም