ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የጤና ስርዓትን ለማሻሻል አበረታች ስራዎችን እያከናወነች ነው - የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የጤና ስርዓትን ለማሻሻል አበረታች ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት(ኦቻ) አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የኢትዮጵያ ኃላፊ ፖል አንቶኒ ሀንዲሊን ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።

መንግስት በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች እያደረገ ላለው ድጋፍ የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤትና ሌሎች የረድኤት ተቋማት አጋርነት ያለው ሚና ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የኢትዮጵያ ኃላፊ ፖል አንቶኒ ሀንድሊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚመሰገን ነው ብለዋል።

በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣውን ቀውስ ለመከላከልና ለመቋቋም በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዓሻራ መርሃ ግብር፣የሴፍትኔት ፕሮግራምና ብሔራዊ የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አድንቀዋል።

በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች በመንግስትና በተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት መካከል ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም