ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሩሲያ ሞስኮ በተካሄደው የብሪክስ አባል ሀገራት የጉምሩክ አስተዳዳሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳተፈች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፣ በሩሲያ ሞስኮ በተካሄደው የብሪክስ(BRICS) አባል ሀገራት የጉምሩክ አስተዳዳሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።

በሩሲያ ሞስኮ ሲካሄድ የነበረው የብሪክስ አባል ሀገራት የጉምሩክ አስተዳዳሪዎች ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡

በጉባኤው በአባል ሀገራቱ መካከል የንግድ ልውውጥን ለማጠናከር፣ ህገ-ወጥ ንግድ እና ድንበር ተሻጋሪ የጉምሩክ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር፣ የቴክኖሎጂ ልህቀትን ለማምጣት፣ የሰው ኃይል ዓቅም ግንባታን ለማጠናከር እንዲሁም የጉምሩክ መረጃዎችን መለዋወጥ በሚቻልበት አግባብ ላይ ውይይት መደረጉም ተገልጿል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ የአባል ሀገራቱ በተናጠል እውቅና የሚሰጧቸው “ልዩ መብት የተፈቀደላቸው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ድርጅቶች” በሌሎች አባል ሀገራትም እውቅና እንዲሰጣቸው እና ተመሳሳይ ጥቅም የሚያገኙበትን አሰራር ለመዘርጋት እንዲቻል የተጀመረውን ስራ ማጠናቀቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ተፈርሟል፡፡

“ልዩ መብት የተፈቀደላቸው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ድርጅቶች” በአለም አቀፍ የንግድ አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑና የተቀመጡ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ሆነው ልዩ መብት የተፈቀደላቸው ድርጅቶች መሆናቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም