በዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 28/2016(ኢዜአ):- በፔሩ ሊማ በተካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል።
ልዑካን ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትና የሚኒስቴሩ የዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉና የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ሌሎችም እንግዶች አቀባበል አድርገውለታል።
ለአትሌቲክስ ልዑካን ቡድኑ ነገ ማለዳ የእውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር እንደሚካሄድም ኢዜአ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከነሐሴ 21 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በፔሩ ሊማ በተደረገው ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 6 የወርቅ፣ 2 የብርና 2 የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎች በማግኘት አሜሪካን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠቀቋ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በሁለቱም ጾታዎች 19 አትሌቶች አሳትፋለች።
የኢትዮጵያ አትሌቶች በሻምፒዮናው በ800፣1500፣ 3000 እና 5000 ሜትር በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በ10000 ሜትር እርምጃ እና በ3000 ሜትር መሰናክል በሴቶች ብቻ ውድድራቸውን አድርገዋል።