የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ  ሚኒስቴር  መዲናዋን  ስማርት ሲቲ ለማድረግ  በትብብር ለመስራት  ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ  ሚኒስቴር  መዲናዋን  ስማርት  ሲቲ ለማድረግ በቴክኖሎጂና በመሰረተ ልማት ስራዎች በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ  ሚኒስቴር መዲናዋን  ስማርት ሲቲ ለማድረግ በቴክኖሎጂና በመሰረተ ልማት ስራዎች በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች  ላይ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) እንዳሉት የመዲናዋ ኢኖቬሽንና  ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ መዲናዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ የጀመራቸው የቴክኖሎጂና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያዎች የሚበረታቱ ናቸው።

የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎች የህዝብን ሀብት በሚገባ በማስተዳደርና ለታለመለት አላማ በማዋል ከተማዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥኑ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ የቢሮውን ሀብትና የሰው ሃይል በማብቃት፣የኢንኩቤሽን ማዕከላትን በማልማት ፣የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን ፣የስማርት ሲቲ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

አካታችና አገር በቀል ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማፋጠን የመሰረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ በትብብርና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ቴክኖሎጂን ማልማት የሚችልና በአግባቡ የሚጠቀም ዜጋን በማፍራትና በዘርፉ የስራ ዕድል በመፍጠር  የአገርን እድገት በሁሉም  ዘርፍ ማፋጠን እንደሚገባም ተገናግረዋል።   

የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን አማረ አዲስ አበባን ወደ ስማርት ሲቲ ለመቀየርና ለዜጎች ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የቴክኖሎጂና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።  

በዚህም በከተማዋ የሚገኙ ቢሮዎችን፣ ክፍለ ከተሞችንና ወረዳዎችን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰርና የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት የሚያስችል ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።

በተጨማሪም የመሬት አስተዳደርን፣ የኮንስትራክሽን ፣የክፍያ ስርዓትንና ሌሎች የቴክኖሎጂና የመሰረተ ልማት ስራዎች ለምተው ወደ ተግባር  መግባታቸውን ተናግረዋል።  

ቢሮው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሰው ሃይሉን በማብቃትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ከተማዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም