ቀጥታ፡

ዘመናትን በተሻገሩ ችግሮች ዙሪያ በመመካከር ሀገራዊ መግባባትና አንድነትን መፍጠር አለብን - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

ሐዋሳ፤ ነሐሴ 28/2016(ኢዜአ)፦ ዘመናትን በተሻገሩ ችግሮች ዙሪያ በመመካከር ሀገራዊ መግባባትና አንድነትን መፍጠር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አስታወቁ።

ኮሚሽኑ በሲዳማ ክልል ያካሄደውን አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ዛሬ አጠናቋል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በማጠናቀቂያ መርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ ዘመናት በተሻገሩ ችግሮቻችን ዙሪያ በመመካከር ሀገራዊ መግባባትና አንድነትን መፍጠር ይገባል።

የተለያየ ሃይማኖት፣ ባህል፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ በሚራመድባት ሀገር ልዩነቶችን መፍታት የሚቻለው በመነጋገርና መደማመጥ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የተጀመረውን የምክክር ሂደት የተሳካ ለማድረግ መደማመጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑም የህዝቡን አጀንዳ ለማድመጥ በትኩረት እየሰራ ነው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በየክልሉ የተመረጡ አጀንዳዎች ተሰብስበውና ተለይተው በሀገራዊው መድረክ ምክክር እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል፡፡

በሂደቱም አካታች በሆነ መልኩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድምጽ እኩል የሚሰማበትን እድል በመፍጠር በመመካከር መግባባት ላይ በመድረስ የምንፈልጋትን ሀገር እንገነባለን ብለዋል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ በክልሉ የተከናወነው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት የተሳካ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በክልሉ አጀንዳ ለማደራጀት ከተመረጡ 25 ሰዎች ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን የወከሉት ወይዘሮ መስተዋት ወልደአማኑኤል በበኩላቸው፤ ሂደቱ ግልጽና ሰፊ ውይይት የተደረገበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የተነሱ በርካታ ጉዳዮችን በማደራጀት መሰረታዊ የሆኑት ለሀገራዊ ምክክሩ እንዲቀርቡ መደረጋቸውን ገልጸው፤ በችግሮቹ ዙሪያ መመካከርና መወያየት በራሱ የመፍትሄ አካል ነው ብለዋል፡፡

ከምክክሩ የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት ሁሉም የመፍትሄ አካል በመሆን ሀገርን መታደግና የመደማመጥ ባህልን ማሳደግ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

ሀገራዊ በሆነው የምክክር ሂደት ተሳታፊ በመሆናቸው መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ አጀንዳ በማደራጀት የተወከሉት አቶ መላኩ በቀለ የአጀንዳ ልየታው ዴሞክራሲያዊና ግልጽ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

አጀንዳ በማደራጀት ሂደትም ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች መዳሰሳቸውንና ወደ ሀገራዊ ምክክር እንዲቀርብ ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ጠቁመዋል።

በመድረኩ የክልሉን አጀንዳ ለማደራጀት የተመረጡ 25 ተወካዮች አጀንዳዎቻቸውን ለዋና ኮሚሽነሩ አስረክበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም