ቀጥታ፡

የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም "ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ይከናወናል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2016 (ኢዜአ)፦ የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም "ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063" በሚል መሪ ሀሳብ ከነገ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ ይከናወናል፡፡

ከነሀሴ 29 ቀን እስከ ጵጉሜ 1 ቀን 2016 የሚከናወነው ፎረም ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን በርካታ ተሳታፊዎች እንደሚታደሙበት ታውቋል፡፡

ፎረሙ የኢትዮጵያ የነጻነት ቀንዲል በሆነው የአድዋ ሙዚየም የሚከናወን ሲሆን ኢትዮጵያ አንደ ሀገር የተለያዩ ጥቅሞችን እንደምታገኝበት ይጠበቃል፡፡

በፎረሙ ከ 47 በላይ የአፍሪካ ሀገራት፣ ከ30 በላይ የተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከመላው አለም የተውጣጡ ከ 1ሺ 500 በላይ ታዳሚዎች በፎረሙ ላይ እንደሚታደሙ ማወቅ ተችሏል፡፡

በመድረኩ የኢትዮጵያ ከተሞች ተሞክሯቸውን በማጋራት ከአቻ የአፍሪካ ከተሞች ልምድ እንደሚቀስሙ የሚጠበቅ ሲሆን አጋጣሚውን በመጠቀም ራሳቸውን የሚያስተዋወቁበት ዕድል ተመቻችቶላቸዋል፡፡

የፎረሙ ታዳሚዎች በአዲስ አበባ የተገነቡ ሜጋ ፕሮጀክቶችንና የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንደሚጎበኙም ይጠበቃል፡፡

ፎረሙ የራሱ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞችን የሚያስገኝ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በተለይም የከተማዋ ነዋሪዎች እንግዶቹን በተለመደው ጨዋነት እንዲቀበልም ጥሪ ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም