ቀጥታ፡

የአዋጭነት ጥናታቸው የተጠናቀቁ 101 የፈጠራ ሃሳቦችን ከአዲሱ አመት ጀምሮ ፋይናንስ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል-የኢትዮጵያ ልማት ባንክ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2016(ኢዜአ)፦ የአዋጭነት ጥናታቸው የተጠናቀቁ 101 የፈጠራ ሃሳቦችን ከመስከረም 2017 ጀምሮ ፋይናንስ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስታወቀ።

ከወራት በፊት በተካሄደው የ''ስታርት አፕ ኢትዮጵያ'' ፎረም ላይ መንግስት ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን /ስታርታፖችን/  በተሻለ ህግና የአሰራር ስርዓት ለመደገፍ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መግለፃቸው ይታወቃል።

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በኢትዮጵያ ስታርትአፕ ብዙም ትኩረት እንዳልተሰጠው አስታውሰው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት መንግስት ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ገልፀዋል።

ከለውጡ በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ50 የማይበልጡ ስታርታፖች የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ከ900 በላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። 

የባንኩ ፕሬዝዳንት ዮሃንስ አያሌው(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት ባንኩ ባለፉት አምስት አመታት ባደረገው ሪፎርም ከኪሳራ በመውጣት በሀገሪቱ ካሉ ባንኮች በካፒታል አቅሙ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

ባንኩ አጠቃላይ ሃብቱን 182 ቢሊየን ብር ማድረሱን ገልፀው በሀገሪቱ የሚገኙ የግብርና፣ አምራችና ኢንዱስትሪ ዘርፎችን ፋይናንስ በማድረግ ለኢንቨስትመንት አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ባንኩ በተጠናቀቀው በጀት አመት በራሱ 5ሺህ 600 እንዲሁም በካፒታል ሊዝ ፋይናንስ ተቋማት በኩል 1 ሺህ 800 ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ማስገባቱን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ ከ600 በላይ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች ለባንኩ የፋይናንስ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልፀው ከእነዚህ ውስጥ 101 ለሚሆኑት ጥያቄዎች የአዋጭነት ጥናት መጠናቀቁን አስረድተዋል።

በዚህም ከመስከረም 2017 ጀምሮ የፈጠራ ሃሳብን ፋይናንስ ለማድረግ በባንኩ በኩል ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ለፈጠራ ስራ ባለቤቶች በሰመር ካምፕና በተለያየ መንገድ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በባንኩ የአዋጭነት ጥናታቸው ከተጠናቀቁት 101 ፕሮጀክቶች አብዛኞቹ የዚህ ውጤት ናቸው ብለዋል።

ባንኩ የጤና ዘርፉን በፋይናንስ በመደገፍ ሀገሪቱን የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የተሻለ ህክምና ለማግኘት ወደ ውጭ ሀገራት የሚሄዱ ሰዎች በሀገር ውስጥ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ከባለድርሻዎች ጋር በመቀራረብ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለዚህ ስኬት በተለያዩ አካባቢዎች ፋይናንስ የተደረጉ የጤና ፕሮጀክቶች መኖራቸውን በመግለፅ።

በቀጣይ በተለይ በተርሸሪ ደረጃ ለህብረተሰቡና ለሌሎች ሀገራት ጭምር አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የጤና ተቋማት እንዲገነቡ ለማስቻል እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም