የዓለም እና የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት መልካም እድልን የሚሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም እና የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት መልካም እድልን የሚሰጥ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚያደርጋቸው የዓለም ዋንጫና የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት መልካም እድልን የሚሰጥ መሆኑን የፊፋ ቴክኒክ ኤክስፐርትና የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ገለጸ።
ብሔራዊ ቡድኑ እ.አ.አ በ2026 አሜሪካ፣ ካናዳና ሜክሲኮ በጣምራ ለሚያዘጋጁት 23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በአፍሪካ ዞን በምድብ አንድ ከግብፅ፣ ከጊኒ ቢሳው፣ ቡርኪናፋሶ ፣ሴራሊዮንና ጅቡቲ ጋር መደልደሉ የሚታወስ ነው።
ብሔራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሦስት ጨዋታ አቻ ወጥቶ፣ በአንድ ጨዋታ ተሸንፎ በሦስት ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ድልድል የዕጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ይፋ ከተደረገ በኋላ ደግሞ በማጣሪያው የሚሳተፉ ሀገራት ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በምድብ ስምንት ከጊኒ ፣ታንዛኒያና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ተደልድሏል።
ቡድኑ ነገ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ዳሬሰላም ላይ ከታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደርጋል።
የፊፋ ቴክኒክ ኤክስፐርትና የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ብሔራዊ ቡድኑን አስመልክቶ ያለውን ምልከታ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ አጋርቷል።
የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የዓለም ዋንጫና የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት መልካም እድልን የሚሰጥ ነው ብሏል።
ይህን ምቹ አጋጣሚ ብሔራዊ ቡድኑን ለመገንባት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።
ለብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ በቂ ጊዜ መስጠት እንደሚገባና የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ተጨዋቾችን በተወሰነ የጊዜ ርቀት ስለሚያገኝ የወዳጅነት ጨዋታዎች እንደሚያስፈልገው አመልክቷል።
ቡድኑ በቂ የመቀናጃ ጊዜና የወዳጅነት ጨዋታዎችን ካገኘ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያለውን እምነት ገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ፤ ሁለተኛና የሜዳ ጨዋታውን ጷጉሜን 4/2016 ዓ.ም ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ዳሬሰላም ላይ ጨዋታውን ያደርጋል።
በ2026 አሜሪካ ካናዳና ሜክሲኮ በጣምራ አዘጋጅነት ለሚያከናውኑት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀጣይ ጨዋታውን ከግብፅ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያከናውናል።