ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ያቋረጠበትን ምክንያት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ያቋረጠበትን ምክንያት ይፋ አደረገ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ወደ አስመራ የሚደረገው በረራ የተቋረጠበትን ምክንያት በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

አየር መንገዱ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ እንዳይቋረጥ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከዛሬ ጀምሮ ለማቋረጥ መገደዱን ገልጸዋል።

የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አየር መንገዱ ወደ አስመራ የሚያደርጋቸውን በረራዎች በተመለከተ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት በጎ እርምጃዎች እንደተወሰዱና በቂ ምላሽ እንደተሰጠውም አውስተዋል።

አየር መንገዱ ዳግም ወደ አስመራ በረራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት 6 ዓመታት ኤርትራውያንን ከኢትዮጵያ ብሎም ከመላው ዓለም በአየር ትራንስፖርት ሲያስተሳስር የቆየ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አየር መንገዱ ከኤርትራ በኩል በረራውን ለማቋረጥ ገፊ ምክንያት የሚሆኑ ችግሮች እንዳጋጠሙት ተናግረዋል።

ለአብነትም አየር መንገዱ የሽያጭ ገቢውን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይልክ የኤርትራ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን የእግድ ደብዳቤ መጻፉን ሂሳቡ የተከፈተበት የባንክ ቅርንጫፍ መግለጹንና ችግሩን ለመፍታተ ለአንድ ወር ጥረት መደረጉን አንስተዋል።

አየር መንገዱ አገልግሎቱን መስጠቱን በመቀጠል ባንኩ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ገንዘቡን መያዝ እንደሌለበት በመግለፅ እንዲለቀቅለት ሲጠይቅ መቆየቱንም ጠቅሰዋል።

ከአንድ ወር በላይ ገንዘቡን ማውጣት እንዳልቻለ ገልጸው፥ ለኤርትራ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣንም ገንዘቡ እንዲለቀቅና መወያየት እንደሚገባ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ጠቅሰዋል።

ሆኖም አየር መንገዱ ምንም ዓይነት ምላሽ ባያገኝም መንገደኞቹን ማገልገሉን እንደቀጠለ በማንሳት፥ ሆኖም ባለፈው ቅዳሜ የሽያጭ ገቢውን ወደ ባንክ ለማስገባት ሲሞክር የባንክ ሂሳቡ ሙሉ በሙሉ መታገዱን እንደተገለጸላቸውና ደብዳቤም እንደተጻፈላቸው አንስተዋል።

ይህም አየር መንገዱ በአስመራ ኤርፖርት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶችና ለሰራተኞች ደመወዝ ክፍያ መፈጸም እንዳይችልና ሂሳቡን እንዳያንቀሳቅስ የሚያደርገው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም አየር መንገዱ በእነዚህና ሌሎች ከኤርትራ በኩል ባጋጠሙት ተደጋጋሚ ችግሮች ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ማቋረጡን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም