ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ተከናውነዋል- አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ተከናውነዋል- አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2016 (ኢዜአ)፡- ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት መከናወናቸውን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
“ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በአርባ ምንጭ የሚከበረው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴ በዝግጅቱ መሪ ዕቅድ ላይ ውይይት አድርጓል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እንዳሉት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
እውነተኛ የፌደራል ስርዓትን ለማፅናት በሚደረገው ሂደት የማንነትና የአደረጃጀት ጥያቄዎች የህዝብን ተሳትፎ በሚያረጋግጥ መልኩ ምላሽ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።
ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሕዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት ወሳኝ መሆኑንም አቶ አገኘሁ አስረድተዋል።
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር የዜጎችን ሕብረብሔራዊ አንድነት በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበርም አመላክተዋል።
በፌደሬሽን ምክር ቤት የመንግስታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና የህገ መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ባንቺይርጋ መለሰ ነባራዊ ሁኔታዎችን በመገምገም የአከባበሩ እቅድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በዓሉ የኢትዮጵያውያንን ህብረ ብሔራዊ አንድነት በሚያጸና መንገድ እንደሚከበር ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፀሐይ ወረሳ ክልሉ የበዓሉ አስተናጋጅ እንደመሆኑ በቂ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን አፈጻጸሙም በየሳምንቱ እየተገመገመ ነው ብለዋል።
በዓሉ ክልሉ ያለውን እምቅ አቅም የሚያስተዋውቅበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች እቅዱ ለበዓሉ አከባበር ትልቅ አቅም የሚፈጥር እና መሪ ቃሉም ጊዜውን የዋጀ መሆኑን አንስተዋል።
የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች ለበዓሉ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው እና በትምህርት ተቋማት በስፋት ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዝያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም ባካሔደው 2ኛ መደበኛ ጉባዔው "ሕዳር 29" የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰኑ ይታወቃል።