ቀጥታ፡

ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ትራንስፎርሜሽን የአገሪቱን የአቪዬሽን መስክ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 28/2016 (ኢዜአ)፡- የአቪዬሽን መስኩን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ትራንስፎርሜሽን ተግባራዊነት ወሳኝ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዳንጌ ቦሩ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በአቪዬሽን መስክ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግራትን ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ትራንስፎርሜሽን መርኃ ግብር ይፋ አድርጓል።

በመርኃ ግብሩ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዳንጌ ቦሩ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግሥቴን ጨምሮ ሌሎችም የዘርፉ ተወካዮች ተገኝተዋል።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዳንጌ ቦሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው መሪነቷን በዘላቂነት ለማስቀጠል ሁሉን አቀፍ ለሆነ የዘርፉ መዘመን ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።

የአቪዬሽን  ኢንዱስትሪ  እድገት መሰረት ደኅንነት በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት መደረጉን አንስተው ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ትራንስፎርሜሽን መርኃ ግብር ዘርፉን በላቀ ቴክኖሎጂ የማስቀጠል ትልም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን መስክ ሰፊ የቴክኖሎጂ ሽግግርና እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ አንጻር  በኢትዮጵያ የአቪዬሽን መስኩን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ትራስፎርሜሽን ተግባራዊነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው መርኃ ግብሩ አገሪቱ እያደገ የመጣውን የአቬይሽን ፍላጎት ምላሽ ለመሰጠትም ያሰችላል ብለዋል። 

በመጪው ጊዜም ቴክኖሎጂን ማዕከል ያደረገ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ደኅንነትን የማስጠበቅ ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት።


 

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተር ጌታቸው መንግሥቴ በበኩላቸው፣ ብሔራዊ የአቪዬሽን ትራንስፎርሜሽን መርኃ ግብር ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ደኅንነት የላቀ ተግባር ለማከናወን ቁርጠኛ መሆኗን የሚያመላክት ነው ብለዋል። 

ይህ ትራንስፎርሜሽን እያደገ የመጣውን የአቪዬሽን መስክ መሰረት በማድረግ ዘርፉ የሚጠይቀውን አሁናዊ ቁመና ለመላበስ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በመጪው ጊዜያት ከዓለም አቀፍ ኦፕሬተሮች ቀላል የማይባል ውድድር ይጠብቀናሰል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ባለሥልጣኑ ይህንኑ ትራስፎርሜሽን እውን ለማድረግ ላለፉት 2 ዓመታት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ነው ያነሱት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም