የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል ያካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል ያካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተጠናቀቀ
ሀዋሳ፤ነሐሴ 28/2016 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል ያካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተጠናቀቀ።
የክልሉን አጀንዳ ለማደራጀት የተመረጡ 25 የህብረተሰብ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት የክልሉን አጀንዳ ለኮሚሽኑ አስረክበዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በወቅቱ እንደገለጹት፤ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችና ልዩነቶች ግጭትና ዘርፈ ብዙ ጉዳት አስከትለዋል።
የተለያዩ ምእራፎች ያሉት የኮሚሽኑ ስራ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ሂደቱም የተሳካ መሆኑን ተናግረዋል።
የሲዳማን ክልል አጀንዳ አደራጅተው ለኮሚሽኑ ያቀረቡ ተወካዮችን ያመሰገኑት ዋና ኮሚሽነሩ፤ "ለሀገርና ለህዝብ በሚጠቅሙ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ሀገራዊ ሃላፊነታችሁን ተወጥታችኋል" ብለዋል።
"በየክልሎቹ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች በምክክር ኮሚሽኑ ተለይተው መሰረታዊ የሆኑ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ላይ ተወያይተን ወደ ትግበራ ምእራፍ እንዲሸጋገሩ በትኩረት እንሰራለን" ብለዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ ከኮሚሽኑ አማካሪ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የክልሉን አጀንዳ ተረክበዋል።
ኮሚሽኑ ነሃሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም የክልሉን አጀንዳ ማሰባሰብ ስራ የጀመረ ሲሆን ዛሬ አጠናቋል።