በክልሉ የ2017 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት መስከረም 6 ቀን ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የ2017 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት መስከረም 6 ቀን ይጀመራል
መቀሌ ፤ ነሐሴ፤28/2016 (ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል የ2017 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ እንደሚጀመር በጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ገለፀ።
በክልሉ ከ450 በላይ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዕሽ እንደገለፁት፤ መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም በክልሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኛሉ።
የትምህርት ዘመኑ የምዝገባ ሂደት ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ መጀመሩን የተናገሩት ኃላፊው፤ ጥራትን በማረጋገጥ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ መምህራን፣ የትምህርት አመራር አባላትና ወላጆች ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በዚህ መሰረት የ2017 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት መስከረም 6 ቀን በይፋ እንደሚጀመር ገልጸዋል።
የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥን ለመቀነስም በትምህርት ቤቶች የተጀመረው የምገባ መርሃ ግብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል።