ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ትራንስፎርሜሽን መርኃ ግብር ይፋ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ትራንስፎርሜሽን መርኃ ግብር ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ፤28/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በአቪዬሽን መስክ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግራትን ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ትራንስፎርሜሽን መርኃ ግብር ይፋ አድርጓል።
በመርኃ ግብሩ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዳንጌ ቦሩ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግሥቴን ጨምሮ ሌሎችም የዘርፉ ተወካዮች ተገኝተዋል።
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዳንጌ ቦሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው መሪነቷን በዘላቂነት ለማስቀጠል ሁሉን አቀፍ ለሆነ የዘርፉ መዘመን ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።
የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ እድገት መሰረት ደኅንነት በመሆኑ ለዘርፉ የላቀ እድገት ትኩረት መደረጉን አንስተው ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ትራንስፎርሜሽን መርኃ ግብር ዘርፉን በላቀ ቴክኖሎጂ የማስቀጠል ትልም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በመጪው ጊዜም ቴክኖሎጂን ማዕከል ያደረገ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ደኅንነትን የማስጠበቅ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተር ጌታቸው መንግሥቴ በበኩላቸው፣ ብሔራዊ የአቪዬሽን ትራንስፎርሜሽን መርኃ ግብር ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ደኅንነት የላቀ ተግባር ለማከናወን ቁርጠኛ መሆኗን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ይህ ትራንስፎርሜሽን እያደገ የመጣውን የአቪዬሽን መስክ መሰረት በማድረግ ዘርፉ የሚጠይቀውን አሁናዊ ቁመና ለመላበስ የሚያስችል ነው ብለዋል።