ስልጠናው በዲጅታል ቴክኖሎጂ የተሻለ ክህሎት እንድናገኝ እያስቻለን ነው - ተሳታፊዎች

ሐረር ፤ነሐሴ 28/2016(ኢዜአ):-  የኢትዮጵያን ኮደርስ ዲጂታል ስልጠና በቴክኖሎጂው የተሻለ ክህሎት እንድናገኝ እያስቻለን ነው ሲሉ በሐረሪ ክልል ስልጠናውን እየተከታተሉ የሚገኙ ወጣቶች ገለጹ።

በሐረሪ ክልል ከ1ሺህ 500 በላይ ወጣቶች የኢትዮጵያን ኮደርስ ዲጂታል ቴክኖሎጂን እየሰለጠኑ ይገኛሉ።

ስልጠናውም በዘርፉ የተሻለ ክህሎት እንዲያገኙ እያስቻላቸው መሆኑን ነው ለኢዜአ የገለጹት።

ከሰልጣኞቹ መካከል በዌብሳይት ዲዛይን ስልጠና እየወሰደች የምትገኘው ወጣት ሳምራዊት ዓለሙ እንደገለፀችው ስልጠናው ቀደም ሲል ከነበራት የቴክኖሎጂ እውቀት የተሻለ ክህሎት እያስገኘላት መሆኑን ተናግራለች።


 

ዘመኑ የቴክኖሎጂ ዘመን ነው የምትለው ወጣት ሳምራዊት፤ ለወጣቱ እንደዚህ ዓይነት ስልጠናዎችን መስጠት አገሪቷ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እያከናወነች የምትገኘውን ስራ ለማጎልበት ትልቅ አስተዋጽዎ እንደሚያደርግ ገልጻለች።

ስልጠናው በክረምቱ ወቅት መሰጠቱ የእረፍት ጊዜያቸውን አልባሌ ስፍራ ከማሳለፍ ይልቅ በስልጠና እንዲያሳልፉ እድል መፍጠሩን የተናገረው ደግሞ  በዳታ ቤዝ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ስልጠና እየወሰደ የሚገኘው ሌላኛው ወጣት ዮናታን ብርሃኔ  ነው።


 

ዓለም ዲጂታላይዝድ እየሆነች ነው የሚለው ወጣት ዮናታን፤ ወጣቱም በተለይ ስለኮንፒዩተር ግንዛቤ መኖር የግድ ስለሆነ ስልጠናው በኮንፒዩተርና በዲጂታላይዜሽን የተሻለ ክህሎት እንድናገኝ እያስቻለን ነው ሲል ገልጿል።

በክረምቱ ወቅትይ ያለ ሥራ እቤት ተቀምጦ እንደነበር የሚናገረው የዌብ ፕሮግራሚንግ ሰልጣኝ ወጣት ዐቢይ መርጊያ ስልጠናው የእረፍት ጊዜያችንን በአግባቡ እንድንጠቀምበት አስችሎናል ብሏል።


 

በተለይ በቀጣይ የመደበኛ የትምህርት ጊዜው የሚማረውን የዌብ ፕሮግራሚንግ ትምህርት በኮዲንግ ስልጠናው  አስቀድሞ  በማግኘቱ መደሰቱን ጠቁሞ መንግስት እንደዚህ ያሉ ስልጠናዎችን ማብዛት እንደሚገባውና ወጣቱም እድሉን እንዲጠቀምበት አስተያየት ሰጥቷል።

ከዚህ ቀደም የኮደርስ እውቀት እንዳልነበራትና አሁን እየወሰደችው በሚገኘው ስልጠና የተለያዩ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት እያገኘች መሆኑን የጠቀሰችው ደግሞ በአንድሮይድ ዴቨሎፕመንት ስልጠና እየወሰደች የሚትገኘው ወጣት አሚና መመድ ናት።


 

ባገኘችው እድል መደሰቷን የገለጸችው ወጣት አሚና፤ እንደዚህ ዓይነት ስልጠናዎች ወጣቱን የሚጠቅሙ በመሆኑ ሊስፋፉ ይገባል ስትል ጠይቃልች።

ሀገሪቷ ዲጅታል ስትራቴጂን ቀርጻ ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ስራ መገባቱንና  ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለዘመኑ ወጣት አስፈላጊ በመሆኑ ስልጠናው የሚሰጥ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሐረሪ ክልል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ሃላፊ አቶ ጀማል ኢብራሂም ናቸው።


 

እንደ ክልልም ዲጂታል ሐረሪን ከመገንባት አኳያ ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ወሳኝ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ከ1ሺህ 500 በላይ ወጣቶች ስልጠናውን እየተከታተሉ መሆኑን ጠቁመው በዓመቱም 9ሺህ እንዲሁም በሶስት ዓመት 27ሺህ ወጣቶችን ለማሰልጠን እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም