በሸገር ከተማ አስተዳደር በመጪው መስከረም የሚከበሩ በአላት ዝግጅት ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ አስተዳደር በመጪው መስከረም የሚከበሩ በአላት ዝግጅት ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው

ነሐሴ፤በ28 ቀን 2016 (ኢዜአ)፡-በሸገር ከተማ አስተዳደር በመጪው መስከረም የሚከበሩ በአላት ዝግጅት ላይ ያተኮረ ውይይት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር እየተካሄደ ነው።
ውይይቱ "ሰላማችን በጋራ ጥረታችን ይረጋገጣል" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ሲሆን የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ከንቲባው በውይይቱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በከተማ አስተዳደሩ በዓላቱ የህዝቡን ባህል እና ማንነት በሚያንፀባርቅ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።
ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) አክለውም በዓላቱ ሰላማዊነታቸው በተጠበቀ መልኩ እንዲከበሩ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
የሁሉ ነገር መሰረት ሰላም መሆኑን ጠቅሰው፤ በዓላቱ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበሩም በየደረጃው ያሉ የጸጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በመሆን ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ዘመን መለወጫ፣ ደመራና የመስቀል በዓል እንዲሁም የኢሬቻ በዓል በወሩ ውስጥ በተከታታይ ይከበራሉ።
የበዓላቱ አከባበር በከተማ አስተዳደሩ በየደረጃው ውይይት ሲደረግ የቆየ መሆኑን አንስተው፤ ዛሬም በከተማ ደረጃ የሚደረገው ውይይት በዓላቱን በሰላም ለማክበር የጋራ መግባባት ለመፍጠር መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሁሉም በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎች የድርሻቸውን እንዲወጡም በብልጽግና ፓርቲ የሸገር ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አብዱልአዚዝ አብዱሮ ተናግረዋል።