19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 28/2016(ኢዜአ)፡- 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴ ባካሄደው ውይይት 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ እንዲከበር ውሳኔ አሳለፈ፡፡

አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴው በዛሬው እለት ያካሄደውን ውይይት የመሩት ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ሕገመንግሥታዊ መብቶች ለማስከበር፣ ብዝኃነት እንዲጠናከር፣ አብሮነትና ወንድማማችነት ሥር እንዲሰድና በአጠቃላይ ጤናማ የፌዴራል ሥርዓት እንዲጎለብት የሚያግዙ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል ሲሉ ገልጸዋል።

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ ሲከበርም ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር የዜጎችን ሕብረብሔራዊ አንድነት በሚያጠናክር መንገድ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡


 

ያለፉት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር ዜጎች ባህላቸውን እንዲያስተዋውቁ እድል የፈጠረላቸው ቢሆንም በቀጣይ ግን ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለነፃነትና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መከበር በጋራ እንዲቆሙ በሚያስችል መልኩ ማክበር እንደሚገባ አሳስበዋል።

አገራችን የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባለቤት በመሆኗ ሕብረ ብሔራዊ አንድታችንን ጠብቀን ብልጽግናችንን ለማረጋገጥ የሕዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።

በቀጣዩ ዓመት ለውጡን ተከትሎ በአጀንዳነት ተነስተው የነበሩ የሕዝብ ጥያቄዎች ወደ ጠረጴዛ መጥተው ወደ መመካከርና ብሔራዊ መግባባት የሚመጣበት፣ ብሔራዊ መግባባት ላይ በመነሳት አካታች የሆነ ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የምናጠናክርበት እንደሚሆንም አስገንዝበዋላ።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዲሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገመንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ወይዘሮ ባንቺይርጋ መለሰ ሀገር አቀፉን መነሻ እቅድና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አፈጉባዔ ወይዘሮ ፀሐይ ወራሳ ደግሞ ክልላዊ እቅዱን ለአስተባባሪ ኮሚቴው አቅርበዋል።


 


አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴውም የቀረቡለትን እቅዶች ከመረመረና ግብዓት ከአካተተባቸው በኋላ እቅዶችን በማጽደቅ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበር ወስኗል።

ምክር ቤቱ 3ኛው የፓርላማ ዘመን፣ 1ኛው ዓመት የሥራ ጊዜ፣ ሚያዝያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም ባካሔደው 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ሕዳር 29 ቀን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰኑ ይታወቃል፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም