ቀጥታ፡

የሥራና ክህሎት  ሚኒስቴር  በግብርናው  ዘርፍ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተፕራይዞችን ለማደራጀት  እና  ወደ ስራ ለማስገባት  ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር ስምምነት ተፈራረመ 

 አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2016 (ኢዜአ)፡-የሥራና ክህሎት  ሚኒስቴር  በግብርናው  ዘርፍ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን  ለማደራጀትና ወደ ስራ ለማስገባት  ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር ስምምነት ተፈራረመ ።   

ስምምነቱን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሀት ካሚል ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሃንስ አያሌው (ዶ/ር) ጋር  ተፈራርመዋል።   

የአፍሪካ  ልማት  ባንክ  ለስራ ዕድል ፈጠራ  ፋይናንስ የሚያቀርብ ሲሆን  በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራሽ እንደሚሆን ተገልጿል።   


 

የሥራና  ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሀት ካሚል  እንዳሉት፤  ሚኒስቴሩ ሥራ ፈጣሪዎችን በማበረታት  ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ከባንኩ ጋር  በትብብር  እየሰራ ነው።  

ለዚህም ላለፈው አንድ ዓመት ከግማሽ ያህል ሚኒስቴሩ ከልማት ባንክ ጋር በመሆን ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው ስምምነቱ የትብብሩ ፍሬ ነው ሲሉ ተናግረዋል።   

የግብርናው  ዘርፍ  በአሁኑ  ወቅት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን  ጠቅሰው፥ በግብርናው ዘርፍ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በበቂ መጠን የሉም ነው ያሉት።

ስምምነቱ በግብርናው ዘርፍ መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማጠናከር በመስኩ የበለጠ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የሚያስችል ነው ብለዋል።

በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው  ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት ማሳደግ  ትኩረት  እንደተሰጠው ገልጸው  ወጣቶችን  በግብርናው መስክ ወደ ስራ ማስገባት ለወጪ ንግድ እንቅስቃሴው መሳለጥ የላቀ ሚና ይጫወታል ሲሉም ነው የገለጹት።


 


የኢትዮጵያ ልማት  ባንክ  ፕሬዝዳንት  ዮሃንስ አያሌው (ዶ/ር) በበኩላቸው ስምምነቱ የፋይናንስ  አቅርቦት  በማሻሻል ረገድ  ሚናው  ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።      

ባንኩ  ከሚኒስቴሩ  ጋር በመሆን በተያዘው በጀት ዓመት ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት  አስፈላጊውን  ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመዋል። 

ለመርሃ ግብሩ በአጠቃላይ 43 ሚሊዮን ዶላር ሥራ ላይ እንደሚውል የገለጹት የባንኩ ፕሬዝዳንት ባንኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ፋይናንሱን ተደራሽ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።  

የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ዜጎች ሀሳባቸውን ሥራ ላይ በማዋል ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ሁለቱ ተቋማት በትብብር መስራታቸውን እንደሚያጠናክሩም አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም