ቀጥታ፡

አገር አቀፍ የውሃ አስተዳደር መረጃ ስርዓት ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊሆን ነው

 

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2016(ኢዜአ):-በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የውሃ መረጃ አያያዝን ይፈጥራል ተብሎ የታመነበት ቴክኖሎጂ ወደ ስራ ሊገባ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከሰዎች ለሰዎች ፋውንዴሽን ጋር በመሆን አገራዊ የውሃ መረጃ ስርዓት ላይ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ዛሬ አካሄዷል።

በውይይቱ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፣የሰዎች ለሰዎች ፋውንዴሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰባስቲያን ብራንዲስ፣ የክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊዎች፣ባለሙያዎችና የልማት አጋር ድርጅቶች ተሳትፈዋል።

መንግስት ባከናወናቸው ስራዎች ለ74 ሚሊዮን ዜጎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የውሃ ፕሮጀክቶች አስመልክቶ ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ የዘመነ የውሃ አስተዳደር መረጃ ስርዓት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ክልሎች የውሃ አስተዳደር መረጃ ስርዓት ቴክኖሎጂ ተግባራዊነት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰው የባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ሰዎች ለሰዎች ድርጅት በኢትዮጵያ የውሃ ልማትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ላደረገው ድጋፍ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ አቶ አበራ እንደሻው በበኩላቸው ሚኒስቴሩ የውሃ አስተዳደርን አስመልክቶ ወጥ የሆነ የመረጃ ስርዓት ፍሰትን ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ክልሎች በውሃ መረጃ ስርዓት ቴክኖሎጂ ያላቸውን ተሞክሮ ወደ ሙከራ ትግበራ በቅርቡ እንደሚሸጋገር ጠቁመዋል።

የሰዎች ለሰዎች ፋውንዴሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰባስቲያን ብራንዲስ እና የኢትዮጵያ ዳይሬክተር በዛብህ አለም ዘመናዊ የውሃ መረጃ ስርዓትና የቁጥጥር ቴክኖሎጂ አስመልክቶ የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በውይይቱ ላይ የመረጃ ስርዓት ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ የሚደረግባቸውን ሳይቶች ለመምረጥ የሚያስችሉ መመዘኛዎች ይፋ ሆነዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከሰዎች ለሰዎች ፋውንዴሽን ቴክኖሎጂውን ለመተግበር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

የቴክኖሎጂ ትግበራውን የሚከታተል የጋራ ቴክኒካል ቡድን እንደሚቋቋምና በየክልሎቹ ተወካዮች እንደሚመደቡ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም