በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መጠን ይኖራል- የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 27/2016 (ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት 10 ቀናት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መጠን ስለሚኖር የጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

በመደበኛ ሁኔታ በቀጣዮቹ 10 ቀናት የክረምቱ ዝናብ በስርጭትም ሆነ በመጠን ከምሥራቅ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀስ በቀስ የመቀነስ አዝማሚያ እንደሚያሳይ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡

በአንጻሩ በመካካለኛው፣ በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ጠንካራ እና የተስፋፋ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖር ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በመካከለኛው፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በ24 ሠዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራል ተብሏል፡፡

በአጠቃላይ በምሥራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉአባቦር፣ ጅማ፣ ባሌ፣ ምሥራቅ ባሌ፣ አዲስ አበባ፣ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን እና ዋግኽምራ ዞኖች በበርካታ ቦታዎቻቸው ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ነው የተባለው፡፡

እንዲሁም መተከል፣ አሶሳ፣ ካማሺ እና የማኦኮሞ ልዩ ዞን፣ የኢታንግ ልዩ ዞን፣ ኑዌር፣ አኝዋ እና ማጃንግ ዞኖች፣ ስልጤ፣ ጉራጌ እና ምዕራብ ጉራጌ ዞኖች፣ ቀቤና፣ ጠምባሮ እና ማረቆ ልዩ ወረዳዎች፣ ሀላባ፣ ሀዲያ፣ የም ዞኖች፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዲኦ እና ወላይታ ዞኖች፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ ኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች፣ ሁሉም የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የምሥራቅ፣ የደቡብ ምሥራቅ፣ የማዕከላዊ፣ የሰሜን ምዕራብ እና የምዕራብ ትግራይ ዞኖች፣ ሐረር እና ድሬዳዋ በበርካታ ቦታዎቻቸው ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች አልፎ አልፎ በፀሐይ ኃይል ታግዞ ከሚፈጠሩ ደመና ክምችቶች ጋር ተያይዞ ነጎድጓዳማ ዝናብ እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም