ቀጥታ፡

በክልሎች አጀንዳ የማሰባሰቡ የእስካሁኑ ሂደት የተሳካ ነው -ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 27/2016 (ኢዜአ) ፡- በክልሎች በመካሄድ ላይ ያለው አጀንዳ የማሰባሰቡ የእስካሁኑ ሂደት የተሳካ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

ዋና ኮሚሽነሩ በሲዳማ ክልል እየተካሄደ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ተገኝተው ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አጀንዳ የማሰባሰቡ ተግባር እስካሁን በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ፣በሐረሪና በጋምቤላ ክልሎች ተከናውኗል።

በክልሎች የሚደረገው አጀንዳ የማሰባሰቡ የእስካሁኑ ሂደት የተሳካ መሆኑን የገለጹት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን፤ በሲዳማ ክልል ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራም ነገ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

በቀጣዮቹ አራት ቀናት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው፤ ይሄው ተግባር በሌሎች ክልሎችም እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም