የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ወደ ታንዛንያ አመራ


አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2016(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ለማድረግ ዛሬ ረፋዱ ላይ ወደ ታንዛንያ አቅንቷል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከታንዛንያና ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ይጫወታል።

የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በመጀመሪያ ዙር ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ ካደረጉ በኋላ ቡድኑ ከነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ  ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ታንዛንያ ከማምራቱ አስቀድሞ የአገር ቤት የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

አሰልጣኝ ገብረመድህን በታንዛንያ በሚደረጉት ጨዋታዎች ላይ የሚጠቀሙባቸውን የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችም ይፋ አድርገዋል።

አማኑኤል ተፈራ፣ አብዱልከሪም ወርቁና ተመስገን ብርሃኑ ከስብስቡ የተቀነሱ ተጫዋቾች ናቸው።

አቤል ያለው፣ አቡበከር ናስርና መስፈን ታፈሰ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ውጪ መሆናቸው ይታወቃል።

አሰልጣኝ ገብረመድህን በተጎዱት የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች ምትክ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩን የፊት መስመር ተሰላፊ አዲስ ግደይ በቡድኑ ውስጥ አካተዋል።

አቡበከር ኑራ፣ሰዒድ ሀብታሙና ፍሬው ጌታሁን በግብ ጠባቂነት ተመርጠዋል።

ሱሌይማን ሀሚድ፣ብርሃኑ በቀለ፣ ያሬድ ባየህ፣ ፈቱዲን ጀማል፣ ሚሊዮን ሰለሞን፣ ፍሬዘር ካሳ፣ረመዳን የሱፍና ያሬድ ካሣዬ በስብስብ ውሰጥ የተካተቱ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች ናቸው።

በአማካይ ክፍል ጋቶች ፓኖም፣ በረከት ወልዴ፣ አብነት ደምሴ፣ ወገኔ ገዛኸኝ፣ ቢኒያም አይተን፣ ቢንያም በላይና ሱራፌል ዳኛቸው ተመርጠዋል።

ቸርነት ጉግሳ፣አዲስ ግደይ፣ ቢኒያም ፍቅሩ፣ ከነዓን ማርክነህና ምንይሉ ወንድሙ በአጥቂ መስመር ክፍል በመጨረሻ ስብስብ ውስጥ የገቡ ተጫዋቾች ናቸው።

ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከታንዛንያ ጋር ነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዳሬ ሰላም ላይ ያካሄዳል።

ሁለተኛና የሜዳ ጨዋታውን ጳጉሜ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ዳሬ ሰላም በሚገኘው ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም (የታንዛንያ ብሔራዊ ስታዲየም) እንደሚያደርግ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

ኢትዮጵያ በማጣሪያው በምድብ 8 ከጊኒ፣ታንዛንያና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር መደልደሏ ይታወቃል።

በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ 48 አገራት በ12 ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

24 አገራት የሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ ይካሄዳል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም