መንግስት ለ2017/18 የምርት ዘመን 25 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ እንደሚፈጽም ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለ2017/18 የምርት ዘመን 25 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ እንደሚፈጽም ገለጸ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 27/2016(ኢዜአ)፡- መንግስት በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለ2017/18 የምርት ዘመን 25 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ እንደሚፈጽም አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ነሐሴ 20 2016 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ለመስኖ እርሻ የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ከመስከረም ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጿል።
በዚህም 25 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ፣ 13 ሚሊየን ኩንታል ዩሪያና 12 ሚሊዮን ኩንታል ዳፕ ግዢ ለመፈጸም የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር መንግስት መፍቀዱን አመልክቷል።
ከ2016 ዓ.ም አንስቶ ተግባራዊ እየሆነ በሚገኘው አዲስ የግዢ መመሪያ አማካኝነት በአፈር ማዳበሪያ ግዢ ላይ የነበሩ ችግሮች መፈታታቸውን ጠቁሟል።
በዚህም ማዳበሪያን ቀደም ብሎ መግዛትና ማጓጓዝ በመቻሉ ባለፈው የምርት ዘመን 21 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን ነው ኮርፖሬሽኑ ያስታወቀው።
በ2016/17 የምርት ዘመን በ930 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከውጭ ከተገዛው 20 ሚሊዮን ኩንታል ያህል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስከ አሁን ከ18 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።
ማዳበሪያው በመሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሮች እየቀረበ ይገኛል።
በ2017/18 የምርት ዘመን ለመስኖ እርሻ የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ለማጓጓዝ የግዢ ሂደት መጀመሩን የግብርና ሚኒስቴር ኮርፖሬሽኑን ዋቢ አድርጎ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።