ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የተጣለብንን ሃላፊነት እየተወጣን ነው - የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊዎች

ሆሳዕና፤ ነሐሴ 26/2016(ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የተጣለብንን ሃላፊነት እየተወጣን ነው ሲሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊዎች ገለጹ።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በሆሳዕና ከተማ እያካሄደ ነው።

በክልሉ በካምባታ ዞን ዶዮገና ከተማ አስተዳደር የመምሀራን ተወካይ አማረች ስዩም ከወከሏቸው የማህበረሰብ ክፍል የተነሱ አጀንዳዎች ላይ በንቃት እየተወያዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በዚህም ሀሳቦች ለኮሚሽኑ ተቀናጅተው እንዲቀርቡ የመለየት ስራ ላይ በመሳተፍ የተጣለብንን አደራ እየተወጣን ነው ብለዋል።

የምክክር ሂደት በሀገሪቱ ዜጎች መካከል ያደሩና ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በማስወገድ ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ለመገንባት ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑን አመልክተዋል።

ከወከሉት ማህበረሰብ የተነሱ አጀንዳዎች ላይ በቡድን እየመከሩ መሆናቸውን ገልጸው በሀገሪቱ ዜጎች መካከል አንድነት እንዲጠናከር የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ መሀመድ ሼይቾ በበኩላቸው በወከሉት ማህበረሰብ የተነሱ ሀሳቦች ላይ በነጻነት እየመከሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም እንደሀገር ላለመግባባታችን መንስኤ ናቸው ተብለው የተለዩ ጉዳዮች በማቅረብ ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲመጣ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ጊዜያት የተዘሩ ህዝብንና ትውልድን የማይመጥኑና ያልበሰሉ ትርክቶች ላለመግባባታችን ምክንያት ናቸው ያሉት አቶ መሀመድ ይህን አስቀርተን አዲስ ምዕራፍ ለመጻፍ ዕድሉን መጠቀም ይገባናል ብለዋል።

ባለን ዕሴትና ልምድ መሰረት ልዩነቶችን በመነጋገር በመፍታት ቀደምት አባቶች ከነክብሯና ዝናዋ ያቆዩልንን ሀገር ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ መመካከር ይገባናል ሲሉ አመልክተዋል።


 

መተኪያ በሌላት በሀገር ጉዳይ ላይ በነጻነት በመነጋገር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ከሚከወን ተግባር በላይ የሚበልጥ ነገር የለም ያሉት ደግሞ በክልሉ የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረትን ወክለው የተገኙት አቶ ተስፋዬ አበራ ናቸው።

በተወከሉበት አካባቢ የተነሱ የማህበረሰብ ሃሳቦችን ጨምሮ ከክልሉ በመጡ ሀሳቦች ላይ እየተወያዩ እንደሚገኙ ጠቅሰው ይህም እንደሀገር ያደሩ ችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ እንዲበጅላቸው የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ከስሜታዊነትና ጊዜያዊ ፍላጎቶች በመውጣት ያለፈውን ታሪክ ከመጪው ማስታረቅ ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።

በዚህም አባቶች ለአንድነትና አብሮነት መጠበቅ የከፈሉትን ዋጋ የሚመጥን አንድነት ገንብተን ሰላሟ የተረጋገጠና የበለጸገች ሀገር ለትውልድ ማሸጋገር ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከትናንት ጀምሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንድ ሺህ 500 ተሳታፊዎች የተካፈሉበት አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባሩን እያከናወነ ሲሆን መድረኩ ለስድስት ቀናት ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም