ምክክሩ ለችግሮቻችን መፍትሄን በማመላከት የተረጋጋ ሃገርን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምን ያረጋግጣል- ባለድርሻ አካላት - ኢዜአ አማርኛ
ምክክሩ ለችግሮቻችን መፍትሄን በማመላከት የተረጋጋ ሃገርን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምን ያረጋግጣል- ባለድርሻ አካላት
ሐዋሳ ፤ነሐሴ 26/2016 (ኢዜአ)፦ የምክክር ሂደቱ ለችግሮቻችን መፍትሄን በማመላከት የተረጋጋ ሃገርን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምን እንደሚያረጋግጥ በሲዳማ ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱን እየተሳተፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት ገለጹ።
4ኛ ቀኑን በያዘው የሲዳማ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የማህበረሰብ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት በቡድን ሆነው በአጀንዳዎቻቸው ላይ እየመከሩ ነው ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማህበራት፣ የተቋማትና የተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተወካዮች እንደገለጹት፤ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ግልጽና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እየተንሸራሸሩ ነው።
በመሆኑም የምክክር ሂደቱ ለበርካታ ችግሮቻችን መፍትሄን በማመላከት የተረጋጋ ሃገርን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወክለው የተሳተፉት የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ በለጠ ሲጌቦ እንደገለጹት፤ ፓርቲያቸው ምክክሩ ሃገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያምናል።
እንደ ፓርቲ እርስ በርስ ያላግባቡንና ሲንከባለሉ የመጡ ሃገራዊና ክልላዊ ጉዳዮችን በማንሳት አጀንዳ የመለየት ስራውን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆን እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
የፖለቲካ ልዩነት ቢኖርም ያለችን አንድ ሃገር ናት ያሉት አቶ በለጠ ሃገራዊ መግባባትንና አንድነትን በሚፈጥሩ ሃሳቦች ላይ የጋራ አቋም ይዘን ለምክክሩ ስኬታማነት የድርሻችንን እያበረከትን እንገኛለን ብለዋል።
የምክክር ሂደቱ ከሃገር አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ውጤትና ትሩፋት ይዞ እንደሚመጣ ዕምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
የሃዋሳ ከተማ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ህይወት ቤላሞ በበኩላቸው መመካከር የችግሮቻችን መፍቻ አንዱ መንገድ በመሆኑ ምክክሩ ለውጥ እንደሚያመጣ እምነት አለን ብለዋል።
በአጀንዳ ልየታውም የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ሂደት እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ በሚያመጡ ሀሳቦች ዙሪያ መወያየታቸውን ገልጸዋል ።
በአጀንዳ ልየታው ወቅት የተለያዩ ሃሳቦች የተነሱ በመሆናቸው የጋራ የሚያደርጉንን ጉዳዮች ነቅሰን ለኮሚሽኑ በማቅረብ ተግባራዊ ውጤት እንጠብቃለን ብለዋል።
ችግር የሚቀረፈው በመወያየት፣ በመነጋገርና በመተሳሰብ በመሆኑ ምክክር አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ወክለው በምክክሩ የተሳተፉት አቶ ጌቱ መታፈሪያ ናቸው።
የአብዛኞቹ ችግሮች ቁልፍ ድህነት መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጪው ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖር የፈጠረውን ግጭት በቡድን ሳይሆን በሀገራዊ ምክክር መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ያለንን በቂ ሃብት ለመጠቀም ሰላምን ማስጠበቅ፣ አንድነትን መጠበቅና በድህነት ላይ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የሴቶች ማህበርን ወክለው በምክክር ሂደቱ እየተሳተፉ የሚገኙት ወይዘሮ አዳነች አለሙ በበኩላቸው በምክክር የሚመራ ቤተሰብ ጠቃሚ ዜጋ እንደሚፈጥር ሁሉ በሃገር ደረጃ መመካከርም ለበርካታ ችግሮቻችን መፍትሄ ለማበጀት ያግዛል ብለዋል።
በተለይም ማህበረሰቡ እንደተወከለበት ጉዳይ በችግሮቹ ዙሪያ እንዲወያይ ዕድል መፈጠሩ መፍትሄውን ለማበጀትና ለውጥ ለማምጣት የተሻለ አማራጭ ስለሆነ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉም ገልጸዋል።
የእምነት ተቋማት የሰላም መሰረት በመሆናቸው ለሰላም፣ ለአንድነትና ለፍቅር እንደሚሰሩ የገለጹት የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርሲቲያን ተወካይ አቶ አሰፋ ኤቲሶ የኮሚሽኑ ስራም ይሄንኑ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ ወቅታዊና በተናጠል ከሚደረጉ ምክክሮች የተሻለ በመሆኑ እንደ ባለድርሻ አካል በምክክር ሂደቱ የህብረተሰቡ አጀንዳ የሆኑ ጉዳዮችን ለይተው በማንሳት ለለውጥ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።