ዕዙ ከህዝቡ ጋር የሚያከናውነውን የሰላምና የልማት ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ - ኢዜአ አማርኛ
ዕዙ ከህዝቡ ጋር የሚያከናውነውን የሰላምና የልማት ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ
ሐረር፤ ነሐሴ 26/2016 (ኢዜአ)፡- በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ ከህዝቡ ጋር የሚያከናውነውን የሰላምና የልማት ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የዕዙ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ ተናገሩ።
የዕዙ 47ኛ ዓመት ምስረታ በዓልን በማስመልከት በዕዙ ቅጥር ግቢ በሚገኘው መሰብሰቢያ አዳራሽ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን በወቅቱም የተለያዩ ጽሁፎች በምሁራንና በባለሙያዎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በጽሁፎቹም በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ ምሥረታና የጦር ሜዳ ተጋድሎ፣ ዕዙ ለአካባቢው ማህበረሰብ በልማት፣ በሰላምና በሌሎች ያከናወናቸው ተግባራት በዝርዝር ቀርበዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ እንደተናገሩት ዕዙ በተለያዩ ጊዜያት የተሰጡትን ተልዕኮዎች በብቃት ሲፈጽምና አንጸባራቂ ድል ሲያስመዘግብ ቆይቷል።
በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ ከሌሎች ክፍሎች ጋር በመሆን ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥሉ ጥቃቶችን በመመከትና ድል በማስመዝገብ ባለፉት 47 ዓመታት ታሪክ ሲያስመዘግብ መቆየቱን አንስተዋል።
በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ በሚሰማራባቸው ግዳጆች በሙሉም ህዝቡን ከጎኑ በማሳለፍም ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወኑን አክለዋል።
የበዓሉ መከበርም ዕዙ ያስመዘገባቸውን ድሎች በመያዝ ቀጣይ ግዳጅን በድል መወጣት የሚያስችል ተጨማሪ አቅም ለመፍጠርና የህዝቡንና የሰራዊቱን አንድነት ይበልጥ አጠናክሮ የማስቀጠል ዓላማ ማንገቡን ገልጸዋል።
በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ ከህዝቡ ጋር የሚያከናውነውን የሰላምና የልማት ስራዎች በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተናግረዋል።
የመከላከያ የቅርስ ጥናትና አስተዳደር ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀኔራል ደሳለኝ ዳቼ በበኩላቸው፤ ዕዙ የሀገር ሉዓላዊነት ከማስከበር ጎን ለጎን የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማጎልበት በግብርና ልማት ስራ የሚያከናውነው ስራ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
በዕዙ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን በመንከባከቡ ረገድም ዕዙ እያከናወነ የሚገኘው ስራም የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
ከፓናል ውይይቱ ቀደም ሲልም በዓሉን በማስመልከት በዕዙ ወታደራዊ ሙዚየም ልዩ ልዩ የዐውደ ውጊያ መሳሪዎችን የሚያሳይ ዐውደ ርዕይ ተከፍቷል።
እስከ ዻጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም በሚቆየው የምስረታ በዓል አከባበር በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ እንዲሁም በሐረር ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን በመመረቅና ሌሎች ፕሮግራሞችም እንደሚከናወኑ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።
በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ እዝ ነሐሴ 21 ቀን 1969 ዓ.ም መመስረቱ ይታወቃል።