በግል የወንጀል አቤቱታዎች ከቀረቡ መዝገቦች 83 በመቶ የሚሆኑት በእርቅ ተፈትተዋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2016(ኢዜአ)፦ በቢሮው ከታዩት 10 ሺህ የሚሆኑ የግል የወንጀል አቤቱታዎች መካከል 83 በመቶ የሚሆኑት በእርቅ መፈታታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ አስታወቀ

በቢሮው የወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አብዮት ጂፋራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የግል አቤቱትና የደንብ መተላለፍ ወንጀሎች አፋጣኝ ፍትህ እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በተለይም ከፖሊስ ጋር በቅንጅት በተሰሩ ስራዎች የምርመራ መዛግብትን ማጥራት፣ በእርቅ መጨረስ፣ ጥፋተኛ የሆኑትን ማስቀጣት ላይ ውጤታማ ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት አመት 12 ሺህ 847 መዛግብት ላይ ምርመራ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከታዩት መዝገቦች ውስጥ 10 ሺህ የሚሆኑት የግል የወንጀል አቤቱታ መያዛቸውንና ከነዚህ መካከል 83 በመቶ የሚሆኑት በእርቅ መፈታታቸውንና የቀሩት በፍርድ ቤት ክርክር እንዲያልቁ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በዚሀም ከ17 ሺህ በላይ ከሳሽና ተከሳሽ ጉዳያቸው ፍርድ ቤት ሳይደርስ በእርቅ እንዲቋጭ መደረጉን አንስተዋል፡፡

በፍርድ ቤት ክርክር 4 ሺህ 91 መዝገቦች ቀርበው 4 ሺህ 33 መዝገቦች ላይ ፍርድ እንደተሰጠና 58 መዛግብት ነጻ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በመነሳት የቢሮው የመርታት አቅም 98 ነጥብ 5 በላይ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

ቢሮው በአስፈጻሚ አካላት የወጡ ህጎችና መመሪያዎች በአግባቡ ተግባር ላይ እንዲውሉ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የልዩ ልዩ ወንጀሎችንና የፍትህ ማሻሻያ ፕሮግራምን በከተማው ተግባራዊ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም