ቀጥታ፡

የባንኩን የተበላሸ ብድር ከ57 በመቶ ወደ 6 ነጥብ 5 በመቶ ማድረስ ተችሏል- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2016(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት አምስት አመታት ባከናወነው ሪፎርም የተበላሸ ብድርን ከ57 በመቶ ወደ 6 ነጥብ 5  በመቶ ማድረስ መቻሉን አስታወቀ።

ባንኩ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት አመት 32 ቢሊየን ብር ብድር መስጠቱና 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱ ተገልጿል። 

የባንኩ ፕሬዝዳንት ዮሃንስ አያሌው (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት ባለፉት አምስት የሪፎርም አመታት ከደንበኛ ጋር ያለውን ግንኙነት ጤናማ በማድረግና የሰራተኞችን ብቃት በማሳደግ ባንኩን ጤናማና ዘላቂ የፋይናንስ አቅም እንዲኖረው ማድረግ ተችሏል። 

በዚህም የባንኩን ካፒታል ከ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በ2016 በጀት አመት ወደ 40 ቢሊየን ብር በማድረስ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ከፍተኛ ካፒታል ያለው ባንክ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባንኩ በአጠቃላይ የነበረበትን የተበላሸ ብድር ከ57 በመቶ ወደ 6 ነጥብ 5 በመቶ ማድረስ መቻሉንም አስረድተዋል።

ባንኩ ከሪፎርሙ በፊት በሊዝ ፋይናንሲንግ ለብድር ያፀድቅ የነበረው 900 ሚሊየን ብር እንደነበር ጠቅሰው በተጠናቀቀው በጀት አመት 27 ቢሊየን ብር ማፅደቁን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ለአምራች ዘርፉ ይፀድቅ የነበረውን ከ 4 ቢሊየን ብር ያልበለጠ በጀት በተጠናቀቀው በጀት አመት ወደ 32 ቢሊየን ብር ማሳደግ መቻሉን ነው የጠቆሙት።

ከሪፎርሙ በፊት በአጠቃላይ ባንኩ ያፀድቅ የነበረው ብድር ከ 10 ቢሊየን ብር እንደማይበልጥ በማስታወስ በተጠናቀቀው በጀት አመት ለብድር አገልግሎት የሚውል 57 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ማፅደቁን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት ባንኩ 16 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር መሰብሰቡን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

ባንኩ ባለፈው በጀት ዓመት ባከናወነው ዘርፈ ብዙ የማሻሻያ ስራ  5 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱንም ገልፀዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም