የስንዴ ልማት የኢትዮጵያን መሻገር ብቻ ሳይሆን የግብርናው ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሻገሩን የሚያመላክት ሆኗል-ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የስንዴ ልማት የኢትዮጵያን መሻገር ብቻ ሳይሆን የግብርናው ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሻገሩን የሚያመላክት ሆኗል-ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2016(ኢዜአ):- የስንዴ ልማት የኢትዮጵያን መሻገር ብቻ ሳይሆን የግብርና ዘርፉ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሻገሩን የሚያመላክት መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እና የክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሎዴ ሄጦሳ ወረዳ መልካ ጀቢ ቀበሌ በ1 ሺህ 800 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የስንዴ ኩታ ገጠም ማሳን ጎብኝተዋል።
በዚሁ ወትት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የስንዴ ልማት የኢትዮጵያን መሻገር ብቻ ሳይሆን የግብርናው ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሻገሩን የሚያመላክት ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።
የስንዴ ልማቱ ግብርናው ወደ ዘመናዊ እርሻ እያደረገ ያለውን ሽግግር እየመራ መሆኑንም በመጥቀስ ዘርፉ ከኋላ ቀር የአስተራረስ ዘዴ በመውጣት ወደ ዘመናዊ እርሻ እየተሻገረ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ፣ የኩታ ገጠም እርሻ፣ የተሟላ የግብዓት አቅርቦትና የመካናይዝድ እርሻ በስንዴ ልማቱ ላይ በተሳካ ሁኔታ መተግበር መቻሉን አስታውቀዋል።
በአገሪቱ ከስንዴ ምርት በአማካይ በሄክታር 36 ኩንታል ማግኘት መቻሉን በማስታወቅ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስንዴ ከሚገኘው አማካይ የምርት ምጣኔ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በመኸር እርሻ ከ 4 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈኑን ገልጸው ከዚህም ውስጥ 70 በመቶው የስንዴ ልማት በኩታ ገጠም የታረሰ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ባስመዘገበችው ውጤታማ ሥራ፤ አሁን ላይ የስንዴ ምርትን ከራሷ አልፋ ወደ ውጪ መላክ የጀመረች ሲሆን ይህም ከአፍሪካ ቀዳሚ ሥፍራ እንድትይዝ አድርጓታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ መንገድ ጀምራለች ያሉት ሚኒስትሩ በዓመት ሦስት ጊዜ ማምረት መቻሉን ጨምረው ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ አሁን ላይ ከራሱ አልፎ የግብርናውን ሽግግር ለማሳለጥ ለወጪ፣ ለተኪና ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ምርቶችን በስፋት እያመረተ ይገኛል ብለዋል።
የግብርናውን ሽግግር ለማፋጠን በቴክኖሎጂ የታገዘ የሜካናይዜሽንን አስተራረስ ዘዴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል ።
በአገሪቱ 20 በመቶ የሚጠጋው የእርሻ ስራ በሜካናይዜሽን እየታረሰ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ግብርናውን ከበሬ ትከሻ ለማላቀቅ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ባለፈው ዓመት 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ዘዴ መታረሱን ጠቅሰው በ2016/17 ምርት ዘመን ምጣኔውን ወደ 12 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
የአርሲ ዞን ሎዴ ሄጦሳ ወረዳ መልካ ጀቢ ቀበሌ አርሶ አደሮች በበኩላቸው የተሟላ ግብዓት በመጠቀም ያመረትነውን የስንዴ ምርት ከራሳችን ፍጆታ አልፎ በብዛት ለገበያ እያቀረብን ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
በኩታ ገጠም በመደራጀት እያመረቱት ያለው ምርት ከዚህ በፊት በተበጣጠሰ ማሳ እያመረቱት ካለው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ተናግረዋል።
አርሶ አደር አየለ ተሰማ እና ሰለሞን ለማ በግብርና ባለሙያዎች ምክር በመታገዝ ከመንግስት የቀረበላቸውን ግብዓት በአግባቡ መጠቀም በመቻላቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡