ቀጥታ፡

አትሌት ሳሮን በርሄ እና አብዲሳ ፈይሳ በዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስገኙ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 25/2016(ኢዜአ)፦ በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የመጨረሻ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ በአትሌት ሳሮን በርሄ እና አትሌት አብዲሳ ፈይሳ ተጨማሪ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

በፔሩ ሊማ ከነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ሻምፒዮና ዛሬ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ተጠናቋል።

በውድድሩ ማብቂያ ቀን የኢትዮጵያ አትሌቶች የተሳተፉባቸው ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሂደዋል።

በሴቶች 1500 ሜትር ፍጻሜ አትሌት ሳሮን በርሄ 4 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ ከ64 ማይክሮ ሴኮንድ አሸናፊ ሆናለች።

በወቅታዊ ብቃቷ ጥሩ አቋም ላይ የምትገኘው አትሌት ሳሮን በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በካሜሮን ዱዋላ በተካሄደው 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወቃል።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ፅጌ ተሾመ 4 ደቂቃ ከ23 ሴኮንድ ከ81 ማይክሮ ሴኮንድ 12ተኛ ወጥታለች።

ካናዳዊቷ አትሌት ራቼል ፎርሳይዝና ጀርመናዊቷ አትሌት ጆላንዳ ካላቢስ ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

በወንዶች 1500 ሜትር ፍጻሜ የተወዳደረው አትሌት አብዲሳ ፈይሳ 3 ደቂቃ ከ40 ሴኮንድ ከ51 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል።

አትሌት አብዲሳ በሻምፒዮናው በ5000 ሜትር የብር ሜዳሊያ ማግኘቱ ይታወቃል።

አውስትራሊያዊው አትሌት ካሜሮን ማየርስና ስፔናዊው አትሌት አሌክስ ፒንታዶ ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የፍጻሜ ውድድር አትሌት ኃይሉ አያሌው 8 ደቂቃ ከ24 ሴኮንድ ከ08 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝቷል።

አትሌት ኃይሉ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት በሪሁን ሞገስ 8 ደቂቃ ከ25 ሴኮንድ ከ45 ማይክሮ ሴኮንድ አራተኛ ወጥቷል።

አትሌት በሪሁን የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቱን ማስመዝገብ ችሏል።

ኬንያውያኑ አትሌቶች ኤድሙንድ ሴሬምና ማቲው ኮስጌይ አንደኛና ሁለተኛ ወጥተዋል።

ኢትዮጵያ የዛሬውን ውጤት ተከትሎ በሻምፒዮናው 6 የወርቅ፣ 2 የብርና 2 የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሯን አጠናቃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም